በምዕራብ ጎጃም ዞን ከ300 የሚበልጡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

133
ባህርዳር ሚያዝያ 22/2010 በምዕራብ ጎጃም ዞን በ43 ሚለዮን ብር ወጭ እየተገነቡ ከሚገኙት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ከ300 የሚበልጡት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ ገለጸ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ የቻለ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በዞኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ከአንድ ሺህ 600 የሚበልጡ የውሃ ተቋማት እየተገነቡ ነው። በመገንብት ላይ ከሚገኙት የውሃ ተቋማት መካከልም የእጅ ውሃ ጉድጓዶች፣ የሚጎለብቱ ምንጮች፣ መካከለኛና ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል። እስካሁንም የ317ቱ የውሃ ተቋማት ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል። በግንባታ ላይ የሚገኙ ቀሪዎቹን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት እስከበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዞኑ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁትና ቀሪ በግንባታ ላይ ያሉት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠናቀው ሲጠናቀቁ ከ200 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡ ይህም የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 74 በመቶ ወደ 85 በመቶ እንደሚያሳድገው ተናግረዋል፡፡ ለንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማቱ ግንባታ ከተመደበው በጀት ውስጥም 18 ሚሊዮን ብር ከህብረተሰቡ የተሰበሰበ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተመደበ መሆኑንም ጠቁመዋል። በዞኑ ጃቢ ጠህናን ወረዳ በሰጎዲት መቅረጫ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ስመኝ ሙሉጌታ አካባቢው የመጠጥ ውሃ ዕጥረት ያለበት በመሆኑ ረጅም ርቀት በመሄድ ንፅህናው ያልተጠበቀ የምንጭ ውሃ በመጠቀም ለተለያየ የውሃ ወለድ በሽታ ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ መንግስት የአካባቢውን ህብረተሰብ አስተባብሮ ምንጩን በዘመናዊ መንገድ ገንብቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ካደረገ ወዲህ ጤናቸው መጠበቁን ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም