ቀጥታ፡

ሃይማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎችን በመተግበር መሆን አለበት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4/2014 (ኢዜአ) ሃይማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ የኮቪድ-19 መከላከያ ዘዴዎችን መተግበር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በዓለማችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ቫይረሱ እራሱን ወደ ተለያዩ ዝርያዎች በመቀየርና ስርጭቱን በማስፋት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት 'ዴልታ' የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በሃገራችን መኖሩ እንደተረጋገጠ ይታወቃል፡፡

ይህ የቫይረስ ዝርያ በስርጭት ፍጥነት ቀደም ብሎ ከነበሩት 'አልፋ' እና 'ቤታ' ዝርያዎች በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮቪድ 19 ምላሽ ዋና አስተባባሪ አቶ አስቻለው አባይነህ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የኮቪድ 19 ዴልታ ቫይረስ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡና በቫይረሱ የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር በሁለት እጥፍ መጨመሩንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በተጨማሪ ወደ ጽኑ ሕሙማን ገብተው ክትትል የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር 751 መድረሱን ጠቁመው፤ ይህም ከ134 ቀናት በኋላ የተመዘገበ ከፍተኛ ቁጥር መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም ቫይረሱ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ችግር ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ሳይዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ጤና ጣቢያዎች በመሄድ ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸውም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለት ሚሊዮን 794 ሺህ 490 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡

በተለይ በቀጣይ ሳምንታት በርካታ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ሃይማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላት ስለሚከበሩ ህብረተሰቡ ለራሱ ፣ለቤተሰቡና ለማህበረሰቡ ጤንነት ሲል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል፡፡ 

ኅብረተሰቡ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም