ቀጥታ፡

በመሠረታዊ ውትድርና ለሁለተኛ ዙር የሰለጠኑ መሰረታዊ ወታደሮች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4/2014 (ኢዜአ) የጦላይ ከፍተኛ ባለ ሌላ ማዕረግተኛ ማስልጠኛ ትምህርት ቤት በመሠረታዊ ውትድርና ለሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ ወታደሮች አስመረቀ፡፡

ትምህርት ቤቱ በተጨማሪ አየር ኃይልን የሚቀላቀሉ መሰረታዊ ወታደሮችን አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ - ስርዓቱ ላይ የመከላከያ ኅብረት የሰው ኃብት ዋና መመሪያ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሀጫሉ ሸለማ እና የማሰልጠኛው ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሎ ተገኝተዋል።

ለምረቃ የበቁት ምልምል ወታደሮች በአገር አንድነት ላይ የሕልውና አደጋ መደቀኑን ተከትሎ የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው የማሰልጠኛ ማዕከሉን መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ያጠናቀቁ ናቸው።

በዚሁ ወቅት ሜጀር ጄኔራል ሀጫሉ ሸለማ መሰረታዊ ወታደሮቹ የአሸባሪ ቡድኑን አገር የማፍረስ ሴራን ለማክሸፍ የመጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"እናት አገራችሁ ያስተላለፈችውን ጥሪ ተቀብላችሁ በመምጣችሁ በታሪክ ፊት ስትታወሱ ትኖራላችሁ" ብለዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በጋራ እየወሰዱት ባለው የማያዳግም እርምጃ አሸባሪው ሕወሃት እንደሚወገድ ገልጸዋል፡፡

ተመራቂዎቹ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በመሰለፍ አሸባሪውን ለማስወገድ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ጡምሲዶ ፈታሎ እንዳሉት፤ መሰረታዊ ወታደሮቹ በውጊያ ቴክኒክ፣ በአካል ብቃትና በሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር የታገዘ  ስልጠና ወስደዋል።

መሰረታዊ ወታደሮቹ በቂ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰዳቸው በየትኛውም ቦታ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት መወጣት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡

ሰልጣኞቹ ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢ በራሳቸው ፍቃድ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የመጡ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም