በአፍሪካ የከይዘን ሽልማት ውድድር ሁለት የኢትዮጵያ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሸናፊ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የከይዘን ሽልማት ውድድር ሁለት የኢትዮጵያ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አሸናፊ ሆኑ
መስከረም 03/2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ የካይዘን ሽልማት ውድድር ሁለት ሆራይዘን አዲስ ጎማ እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሐዋሳ ቅርጫፍ አሸናፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ከይዘን ኢንስቲትዩት እና ሁለቱ አገልግሎት ሰጪና አምራች ድርጅቶች በሽልማቱ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሐዋሳ ቅርንጫፍ እና ሆራይዘን አዲስ ጎማ በከይዘን አሰራር ውጤታማ በመሆን ኢትዮጵያን ወክለው ለውድድሩ መቅረባቸውን ነው የተገለጸው።
በውድድሩም ሆራይዘን አዲስ ጎማ እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሐዋሳ ቅርጫፍ የከይዘን አሰራርን በመዘርጋት ባስመዘገቡት ስኬት የከይዘን ሽልማት ውድድር አሸናፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመኑ ለገሰ ከይዘን ከመተግበሩ በፊት ከፍተኛ የሃብት ብክነት እንዲሁም የሠራተኞችና የደንበኞች እርካታም ዝቅተኛ እንደነበር ገልጸዋል።
የሆራይዘን አዲስ ጎማ የንግድ መምሪያ ሥራ አስኪያጅና የማኔጅመንት ተወካይ አቶ ዳዊት ደምሌ ከይዘን ያለውን አሰራርና የሥራ ባህል ለመለወጥ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
በኤጀንሲው የሐዋሳ ቅርንጫፍ በተደረገው የከይዘን ትግበራ መሰራጨት የነበረባቸውና ስድስት ዓመት ያህል ተከማችተው የነበሩ 107 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች እንዲሰራጩ በማድረግ 34 ሺህ ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል አቶ ዘመኑ።
ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ እየሰራቸው ባለው የላቀ ሥራዎችና ለውጦች ጊዜን በአግባቡ የመጠቀምና የሃብት ብክነትን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
ከይዘንን በመተግበር ሠራተኛው በሥራ ውጤታማ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተገለጹት ደግሞ አቶ ዳዊት ደምሌ ናቸው።
ውጤታማ ከማድረግ በተጨማሪም የከይዘን ትግበራ እንደ ግለሰብም ጭምር ለውጥ ለማምጣት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸው ሽልማቱ ለበለጠ ስራ ያነሳሳናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ከይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ጉዲሳ የከይዘን አሰራር ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
የሽልማቱ ዓላማ ከይዘንን በሚተገብሩ አገራት የሚገኙ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ውጤታማነትን ለማበረታታት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የከይዘን ፍልስፍና የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ የተረጋጋ አመራር አለመኖር፣ እንዲሁም ወጥነት ባለው መልኩ አለመሥራት በተግዳሮትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የከይዘን አሰራርን በተቋማትና ኩባንያዎች ማስፋፋት ከተቻለ የአገር ብልጽግናን ለማፋጠን አጋዥ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲና በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በሚዘጋጀው በዚህ ውድድር ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ከዘጠኝ አገራት የከይዘንን አሰራር በመተግበር 16 የሚሆኑ የተለያዩ ኩባንያ አምራች ድርጅቶች ተወዳዳሪ ሆነዋል።