ለኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ከሁለት ቤት የወጡ አራት ወጣቶች

11

ሰብለ ተከስተ እና ታናሽ እህቷ ትንሳዔ ተከስተ፤ ውልደትና እድገታቸው ጅማ ከተማ ቢሆንም አሁን ላይ እህትማማቾቹ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ይገኛሉ።

"እምቢ ለአገራችን" በማለት ከአንድ ቤት በመውጣት ለኢትዮጵያ የክፉ ቀን ዘብ ለመሆን የተዘጋጁ ሲሆን ኢትዮጵያ የመሸነፍ ታሪክ የላትም ወደ ፊትም በድል አድራጊነቷ ትቀጥላለች ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ እኛ ልጆቿ ላናስደፍራት ቃል ገብተናልና የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ህልውና እንደተከበረ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት ከሃፍረትም በላይ እስከ መጨረሻው ይደመሰሳል ብለዋል የተከስተ ልጆች።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ ገልጸው "መስዋእትነት በመክፈል ለአገራችን ተንሳኤ ተዘጋጅተናል" ነው ያሉት።

በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ያገኘናቸው ወንድማማቾቹ ምስጋናው ጣሜ እና ተመስገን ጣሜ፤ "በእናትና አገር ቀልድ የለም" ይላሉ።

የኢትዮጵያ የህልውና ፈተና ሆኖ የመጣው አሸባሪው ህወሃት በፍጥነት መጥፋት ያለበት ከሃዲ ሃይል መሆኑን ይናገራሉ።

ለዚህም ዘማች ለመሆንና የአገራቸውን ሀልውና ለማስጠበቅ በወላጆቻቸው ተመርቀው ለድል መውጣታቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪውን ድል በማድረግ የአገራቸውን ሰንደቅና ክበር ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውንም ወንድማማቾቹ አረጋግጠዋል።

ከሁለት ቤት የወጡት ወንድማማች እና እህትማማቾቹ ኢትዮጵያን ላለማስደፈርና ክብሯን ለማስጠበቅ ቃል ገብተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም