ቀጥታ፡

የሀገራችንን ህልውና ለማስከበር ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን

ሀዋሳ ፤ መስከረም 3/2014 (ኢዜአ) አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ውስጥ በመሳተፍ የሀገራችንን ህልውና ለማስከበር ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ የብላቴ ምሩቃን ወታደሮች አስታወቁ።

የብላቴ ልዩ ዘመቻዎች ሀይል ማሰልጠኛ ማዕከል በመጀመሪያ ዙር ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ ወታደሮች ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል መሰረታዊ ወታደር ተስፋሁን አይታ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፤ የወታደር ልጅ መሆኑን ጠቅሶ፤ አባቴ መስወዕትነት ከፍሎ ያስረከበኝን ሀገር ህልውናዋ ተረጋግጦ ለልጄ ለማውረስ እሰዋለሁ ብሏል።

በስልጠና ላይ በነበረው ቆይታ ተገቢውን ወታደራዊ ትምህርት እንዳገኘና ለግዳጅ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

መሰረታዊ ወታደር ገነት ተስፋዬ በበኩሏ፤  ከልጅነቷ ጀምሮ ወታደር መሆን ስትመኝ እንደነበር አስታውሳ፤ ዛሬ ይህ ተሳክቶላት ወታደር በመሆን የሀገር ጠላት የሆነውን አሸባሪው ህወሃትን ለመፋለም መነሳሳቷን ተናግራለች።

የሀገራችንን ህልውና ለማስከበር  በሚደረገው ትግል ውስጥ በመሳተፍ  እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ብላለች።

ሌሎችም ወጣቶች ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀላቀል ለሀገራቸው ሉአላዊነት መከበር የድርሻቸውን እንዲወጡ አመልክታለች።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት፤  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ስትራተጂያዊ ስፍራ መገኘቷ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ ሀይሎች አካባቢውን ለመቆጣጠር ሲሉ ሰላም እንዳይኖራት ሲያደርጉ ቆይቷል።

የውጪ ሀይሎች የሀገር ውስጥ የእናት ጡት ነካሾችን በመጠቀም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንድንገባ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።

ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ሲያጋጥሟት የነበረውን ፈተና በልጆቿ ብርቱ ተጋድሎ ማሸነፍ እንደቻለች ያስታወሱት አቶ ደስታ፤ እስካሁን በአንድነቷ ጸንታ የቆየችው ሀገራችን ትፈተናለች እንጂ ተሸንፋ አታውቅም ነው ያሉት።

የእናት ጡት ነካሽ የሆነው አሸባሪው ህወሃትና የጥፋት ተላላኪዎች  የኢትዮጵያ ሀይሎች በመከላከያ ሰራዊቱ አስተባባሪነት በመደምሰስ ተልዕኳቸውን በቁርጠኝነት እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የተመረቃችሁ መሰረታዊ ወታደሮችም በሰልጠናው ያገኛችሁን ዕውቀት በመጠቀም  ይህን አሸባሪ ቡድን  ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

በየጊዜው አቅማችሁን እያጎለበታችሁ  ከጊዜው ቴክኖሎጂ ጋር ራሳችውን በማላመድ የተሻለ ብቁና ተፈላጊ የመከላከያ ሰራዊት አባል ለመሆን መትጋት  ይጠበቅባችኋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ህብረት ሎጅስቲክ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌተናል  ጄኔራል ይመር መኮንን በበኩላቸው፤  መከላከያ ሰራዊታችን በተለያዩ ጊዜያት ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሀገራችንን ሰላምና ደህነነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች  ሲመክት ቆይቷል ብለዋል።

ሰራዊታችን በትግራይ ክልል በቆየባቸው ባለፉት ዓመታት  የክልሉን መንግስትና ህዝብ ከጥቃት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለገንዘቡና ጉልበቱ ሳይሰስት ያበረከታቸው ተግባራት ከግምት ሳይገቡ በአሸባሪው ቡድን አሳፋሪ ክህደት ተፈጽሞበታል ሲሉም አስታውሰዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ ይህ ቡድን ለክህደቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ  ከዙፋኑ ላይ  አውርዶ እንደአይጥ በየጎሬው የሚሽሎከሎክ ተራ አሸባሪ አድርጎታል ነው ያሉት።

ቡድንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከሀገር ጫንቃ ላይ ለማውረድ እኛ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከምንጊዜውም  በላይ ከፍተኛ ተጋድሎ የሚጠይቀን በመሆኑ ዘመኑ በሚጠይቀን መንገድ ይህችን ሀገር ከነሙሉ ክብሯ እንደተረከብን ሁሉ ማስረከብ ይገባናል ብለዋል ሌተናል  ጄኔራል ይመር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም