ቀጥታ፡

ወጣቶች ኢትዮጵያ ያለችበትን ፈታኝ ወቅት አልፋ በሚጻፍ ደማቅ ታሪክ አካል ለመሆን መስራት አለባቸው

መስከረም 3/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያለችበትን ፈታኝ ወቅት አልፋ የሚጻፈው ደማቅ ታሪክ አካል ለመሆን ወጣቶች በያሉበት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት እንዳለባቸው ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት "ዘማች ወጣት" በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ የተሰናዳ የወጣቶች ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታለፉም የተባሉ ችግሮች ገጥመዋት እንዳለፈቻቸው በውይይቱ ላይ ተናግረዋል።

የማታልፈው ኢትዮጵያ እንጂ፤ አስቸጋሪው ፈታኝ ወቅት ያልፋል ሲሉም በንግግራቸው አንስተዋል።

በማታልፈው ኢትዮጵያ ታሪክ ቀደምት አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው የአሁኑ ትውልድ በኩራት አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ የሚያስችል ደማቅ ታሪክ እንዲፃም አድርገዋል ብለዋል።

በተቃራኒው ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ በባንዳነት የተሰለፉ፣ የልጆቻቸውን አንገት የሚያስደፋ ታሪክ መስራታቸውን አስታውሰዋል።

ዲያቆን ዳንኤል አሁንም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማፍረስ የተደቀነባትን ፈተና በማለፍ በሚጻፍ ታሪክ ቀጣዩን ትውልድ አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን የሚያኮራ ታሪክ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ይህ የኢትዮጵያ መከራ ሲያልፍ ለልጅ ልጆቻችን በኩራት የምንነግረው ታሪክ እንዲጻፍ መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ወጣት መሆን ያስፈልጋልም ብለዋል።

የመከላከያ የሕህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነም አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን አገር ክብሯና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እንዲዘልቅ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።

በተለይም ወጣቶች የዚህ ታላቅ አገራዊ ሃላፊነት አደራ አለባችሁ፤ በመደራጀትና በመተባበር የአገር መከታ ልትሆኑ ይገባል ነው ያሉት።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የወጠናቸውን ሴራዎች አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ አገር እንዳትሆን፣ በሕዝቦቿ መካከል አንድነት እንዳይኖር በውጭ ሃይሎችና በውስጥ ከሃዲዎች የጥፋት ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህን እኩይ ዓላማዎች በመመከትና በማክሸፍ በተለይም ወጣቶች ለአገራቸው ነጻነትና እኩልነት በሙያቸው፣ ግንባር ድረስ በመሄድና በሌሎችም ለአገራቸው እንዲዘምቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም