ቀጥታ፡

አገር አቀፉ የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ፕሮጀክት የምዘና ውድድር ከነሐሴ 13 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ይካሄዳል

አዲስ አበባ ነሃሴ 8/2010 ስድስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ፕሮጀክት የምዘና ውድድር ከነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት ይካሄዳል። ከ17 ዓመት በታች እድሜ ባላቸው ታዳጊዎች መካከል በሚደረገው ውድድር ከስድስት ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳድሮች በሁለቱም ጾታዎች በአጠቃላይ 2 ሺህ 101 ስፖርተኞች ይሳተፉበታል። የምዘና ውድድሩ በ17 የስፖርት አይነቶች የሚካሄድ ሲሆን እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ፓራ ኦሎምፒክና መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። ባለፈው ዓመት 13 የስፖርት ዓይነቶች እንደተካሄዱም አስታውሰዋል። ውድድሩ በየዓመቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የታዳጊ ፕሮጀክት የስልጠና ጣቢያዎች ውስጥ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ስልጠና ሲያገኙ የነበሩ ታዳጊ ወጣቶች ብቃት ለመለካት የሚዘጋጅ ነው። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምዘና ውድድሩ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን ክልሉ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል። የትግራይና የሶማሌ ክልሎች በምዘና ውድድሩ ላይ ስለመሳተፋቸው ማረጋገጫ ያልሰጡ ሲሆን ተሳትፎ ስለማድረጉ ካረጋገጡት ውስጥ የደቡብ ክልል ደግሞ የተሳታፊዎችን ስም ዝርዝር እስካሁን አለመላኩን ጠቅሰዋል። በዘንድሮው ውድድር የሚሳተፉ ታዳጊ ወጣቶች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከተሳተፉት 1 ሺህ 945 ተወዳዳሪዎች የተሻለ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት ያጋጥም የነበረውን የእድሜ ተገቢነት ችግር ለመፍታት የፌዴራልና የክልል ባለሙያዎች ተጣምረው የልደት ምስክር ወረቀትን ማጣራት ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች የእድሜ ማጣራት ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል። የምዘና ውድድሩ ተተኪና በቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከተለመደው አሰራር ለመውጣት የሚያግዝ እንደሆነ አቶ ናስር ተናግረዋል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መድረክ በመገናኘት የባህልና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ውድድሩ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስረድተዋል። እስካሁን በተካሄዱት የታዳጊ ምዘና ውድድሮች የተመለመሉ 780 ታዳጊ ወጣቶች በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚና በክልል በሚገኙ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ገብተው ተጨማሪ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የታዳጊ የምዘና ውድድሩ እንዲዘጋጅ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ነገሮችን የማሟላት ስራ እንዳከናወነ ነው አቶ ናስር የጠቀሱት። በኦሮሚያ በሚካሄድው ውድድር የስፖርት ባለሙያዎች ታዳጊዎችን በመመልመል ሌሎች ባለድርሻ አካላት ስፖርተኞችን በማበረታታት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። ስድስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ፕሮጀክት የምዘና ውድድር እስከ ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። አምስተኛው አገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ፕሮጀክት የምዘና ውድድር ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል ሃዋሳ ከተማ የተካሄደ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ በሚገኙ የታዳጊ የስልጠና ጣቢያዎች ለ88 ሺህ 278 ታዳጊ ወጣቶች ዘመናዊ እና ሳይንሳዊ ስልጠና መሰጠቱን ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም