ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ከመጠበቅ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ከመጠበቅ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ አለባቸው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3/2014 ( ኢዜአ) ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ከመጠበቅ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ሃላፊነት አለባቸው ሲሉ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት "ዘማች ወጣቶች " በሚል መሪ ሃሳብ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰናዳው የወጣቶች የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ በመድረኩ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያሴራቸውን ተግባራት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ አገር አንዳትሆን፣ በህዝብ መካከል አንድነት እንዳይኖር በውጭ ሃይሎችና በውስጥ ከሃዲዎች ሙከራዎች በስፋት እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም እነዚህን እኩይ ዓላማዎች በመመከትና በማክሸፍ በተለይም ወጣቶች ታሪካዊ አደራ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ከመጠበቅ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ሃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
ለአገራቸው ህልውና ሲሉ ለፍትህ ለእኩልነትና ለእውነት መታገል ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።
የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፤ አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልንን አገር ከብሯና ሉአላዊነቷ ተጠብቆ እንዲዘልቅ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።
በተለይም ወጣቶች የዚህ ታላቅ አገራዊ ሃላፊነት አደራ አለባችሁ በማለት በመደራጀትና በመተባበር የአገር መከታ ልትሆኑ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ፤ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የጦር ሜዳ፤ የምጣኔ ሃብት፣ የዲፕሎማሲ፣ የሚዲያና ተግባቦት ጦርነት እያንዳንዱ ዜጋ በየአውደ ግንባሩ በመሰለፍ አሸናፊ መሆን አለበት ብለዋል።