ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት ዓለም ዐቀፍ ህግጋትን በመጣስ ህጻናትን በጦርነት እየማገደ ነው--የማህበራዊ ጉዳዮች ተሟጋች ዶረን ኒኮል

መስከረም 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አሸባሪው ህወሃት ዓለም ዐቀፍ ህግጋትን በመጣስ ህጻናትን በጦርነት እየማገደ ነው" ሲሉ የማህበራዊ ጉዳዮች ተሟጋች ዶረን ኒኮል ገለጹ።

ዶረን ኒኮል ካናዳዊ ሲሆኑ ጸሐፊ፣ መምህር እና የማህበራዊ ጉዳዮች ተሟጋች ናቸው። ዶረን ኒኮል ራብል ካ በተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ህወሃት አለምአቀፍ ህግጋትን በጣሰ መልኩ ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየተጠቀመባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለ27 አመታት “ኢህአዴግ” የሚባል ጥምረት ፈጥረው ሃገሪቱን በበላይነት ሲገዙ የቆዩት የህወሃት መሪዎች ስልጣን ማጣታቸውን እንደምክንያት በማድረግ ህጻናትን ለውትድርና በማሰማራት ከመንግስት ጋር ውጊያ መግጠማቸውን አብራርተዋል። በርካታ የትግራይ ዳያስፖራ አባላት መሳሪያ የያዙ ህጻናትን እያሞጋገሱ ህይወታቸው እንዲነጠቅ በማድረግ ላይ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መብቶች ቃልኪዳኖች በተቃራኒ ታዋቂው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አድናቆት ሲሰጠው የነበረውን ምስል በብዙዎች ውግዘት ምክንያት ከገጹ ላይ ቢያነሳውም እውነታው አሁንም መሬት ላይ አለ ብለዋል። ሰብአዊነትን በማስቀደም የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ከትግራይ መውጣቱ ህጻናቱ ለውትድርና እንዲመለመሉና በቀጥታ ጦርነት እንዲሳተፉ ማስቻሉን አንስተዋል።

በትግራይ ክልል ያለ ሁሉ የጦርነቱ ተሳታፊ እንዲሆን የድርጅቱ መሪዎች ትእዛዝ በማስተላለፋቸው ህጻናቱ በብዛት እየገቡ ለመደበኛ ተዋጊዎች ሰብአዊ ጋሻ እንዲሆኑና በማይመለከታቸው ጉዳይ ህይወታቸው እንዲያጡ እያደረገ ነው ብለዋል። ለማንኛውም አላማ ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ የጦር ወንጀል መሆኑን የሚያውቀው የአለም ማህበረሰብ በትግራይ ህጻናት እየረገፉ መሆኑን በአይኑ እያየ ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

አሸባሪ ድርጅቱ በአጎራባች አፋርና አማራ ክልሎች ላደረገው ወረራ የእርዳታ እህል ስርጭትን እንደ መሳሪያ መጠቀሙን ጠቅሰው፤ ህጻን ልጁን ለውትድርና የማይልክ የክልሉ ነዋሪ እርዳታ እንዳያገኝ ከማድረጉም በላይ ለጦርነቱ የሚሰለፉ ህጻናትም አነቃቂ እጽ እንዲወስዱና ራሳቸውን እንዳያውቁ በማድረግ ጉዳት ላይ እየጣላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በብዙ ጉዳዮች ላይ አለሁ ሲል የነበረው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጉዳዩን ጆሮ ዳባ ብሎ ማለፉ ብቻም ሳይሆን ለጋሽ መንግስታትም መግለጫ ለማውጣት ዳተኞች መሆናቸውን አስረድተዋል። እነዚህ አካላት በኡጋንዳ፣ በናይጄሪያና በሱዳን ዳርፉር ተመሳሳይ ድርጊቶች ሲከሰቱ የጮሁትን ያህል አሁን ለምን ማውገዘ እንዳልፈለጉ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የህጻናቱ ለጦርነት መሰለፍና ተጎጂ መሆን በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከመረበሹም በላይ የአለማቀፉ ማህበረሰበ ዝምታ ኢትዮጵያውያን ለምእራባውያን ጥሩ እይታ እንዳይኖራቸው እያደረገ መሆኑን የገለጹት ጸሃፊዋ አሸባሪው ህወሃት ራሱ በለኮሰው እሳት መገረፍ ሲጀምር እንደተጎጂ መወሰዱ ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ስለመስፈኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

የአሜሪካም ሆነ የካናዳ መንግስታት አሸባሪ ካሏቸው ድርጅቶች ጋር እንደማይደራደሩ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስትም ከአሸባሪ ጋር እንደማይደራደር በግልጽ በማሳወቁ ጫና ሊደረግበት እንደማይገባ አጽንኦተ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም