በአዲስ አበባ በሚካሄደው ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ መንግስት በየዓመቱ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚሆን ገቢ እያጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በሚካሄደው ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ መንግስት በየዓመቱ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚሆን ገቢ እያጣ ነው
አዲስ አበባ ነሃሴ 8/2010 በአዲስ አበባ እየተባባሰ በመጣው ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ሳቢያ መንግስትና ህጋዊ ነጋዴዎች እየተጎዱ ህገ-ወጦች ደግሞ አለአግባብ እየበለጸጉ ነው ተባለ። በበዓላት ወቅት በጎዳናዎች ላይ የሚካሄደው የበግና ፍየል ንግድም በመዲናዋ ጽዳትና መልካም ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። የኢትዮጵያ ቁም እንስሳት ንግድ ማህበር፣ ነጋዴዎች፣ ህግ አስከባሪዎች፣ ገቢ ሰብሳቢና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ እንደተገለፀውም የከተማዋ የቁም እንስሳት ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርዓት እያጣ ከመሆኑ ባሻገር ከፍተኛ ህገ-ወጥነት የተንሰራፋበት ሆኗል። በዚህም የዘርፉ ህጋዊ ነጋዴዎች ለኪሳራ እየተዳረጉና መንግስትም ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ ገቢ እያጣ ሲሆን በአንፃሩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችና ተባባሪዎቻቸው ደላሎች ባልተገባ መንገድ እየበለፀጉ መሆኑ ተነግሯል። የቁም እንስሳት ንግድ ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አንተነህ አለሜ እንደተናገሩት አገሪቱ ሰፊ የቁም እንስሳት ኃብት ቢኖራትም የአረባብ ስልቱ በዘመናዊ መንገድ ያልተደገፈና ኋላቀር በመሆኑ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። የመዲናዋ የገበያ ማዕከላት አስፈላጊ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው በመሆናቸው ለግብይትም ሆነ ለቁጥጥር ምቹ አለመሆናቸውን አቶ አንተነህ አስታውቀዋል። የተመቸ የከብቶች ማጓጓዣና የእንስሳት ማድለቢያ ስፍራዎች እጥረትም ተጠቃሽ የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በእንስሳት ንግድ ላይ የተንሰራፋው ህገ-ወጥ አሰራርም ዘርፉ እንዳያድግ ሸብቦ የያዘ ሌላው ማነቆ መሆኑን አቶ አንተነህ አክለዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ መንግስት ህገ-ወጥነትን የሚከላከልበት ጠንካራ አሰራር ባለመዘርጋቱ በገበያው ውስጥ ሀሰተኛ ደረሰኞች በስፋት ይሰራጫሉ፣ ህገወጥ ደላሎችም ገበያውን በመቆጣጠር ያመሰቃቅሉታል። ህገ-ወጥ ንግዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መጥቶ መንግስትን ገቢ ከማሳጣት ባለፈ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ የሚሰራው ነጋዴ ከገበያ እንዲወጣም እያስገደደ ነው ብለዋል። መንግስትም ከዘርፉ በዓመት ሊያገኝ የሚገባውን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እያጣ ነው። የመድረኩ ተሳታፊዎች ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ በበዓላት ወቅት በመዲናዋ ጎዳናዎች የሚካሄደው የበግና የፍየል ገበያ የአስፋልት መንገዶችን፣ የአካባቢን ንፅህናና የነዋሪዎችን ጤና ለአደጋ እየዳረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳምጠው አበበ ችግሮቹን ለመከላከል መንግስት ከምንጊዜውም በላቀ ቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ሆኖም ይህን ህገ-ወጥ ተግባር ማስቀረት የሚቻለው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ከሰሩ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማህበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚያስችለው ቁመና ላይ ሆኖ ህገ-ወጥ ተግባራትን የሚከላከልና ህግ አስከባሪዎችን የሚደግፍ ነጋዴ ለማበራከት መትጋት ይጠበቅበታል ብለዋል።