ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እሄዳለሁ ያለውን የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ማክሸፍ ችለናል - ሜጀር ጀኔራል ክንዱ ገዙ

መስከረም 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እሄዳለሁ ያለውን የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ማክሸፍ ችለናል” ሲሉ ሜጀር ጀኔራል ክንዱ ገዙ ተናገሩ።

የደቡብ ወሎ ዞን በዓልን ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጋር ለማክበር ያዘጋጀው የአዲስ ዓመት የበዓል ፕሮግራም በወሎ ግንባር ተጀምሯል።

በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በግንባር እየተፋለመ የሚገኘውን ሰራዊት አበረታተዋል።

ሜጀር ጀኔራል ክንዱ ፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት፤ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳውን አሸባሪው የህወሀት ቡድን ፍላጎት በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ብርቱ ትግል ከሽፏል።

የመከላከያ ሰራዊት መላ ህዝቡን አሰልፎ የመጣውን የሽብር ቡድን በገባበት ሁሉ በመቅበር ባለበት እንዲቆም እንዳደረገውም ገልጸዋል።

“የሽብር ቡድኑ ህፃናትን በማሰለፍ በብዙ የህዝብ ቁጥር ፍላጎቱን ለማሳካት ቢጥርም በጀግናው ሰራዊታችን ሽንፈትን ቀምሶ ተመልሷል” ብለዋል።

“በጥቂት ቀናት የሰራዊቱ የሰው ሀይልና ግብዓት አቅም እየተጠናከረ በመምጣቱ የሽብር ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች ወሰን ላይ ተቀብሮ እንዲጠፋ እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ የሽብር ቡድኑና አስተሳሰቡ ጠፍቶ የኢትዮጵያ ህዝብ አስተማማኝ ሰላም እንደሚያገኝ ገልጸው፤ አሸባሪው ህወሃት የሰላም ጸር ሆኖ እንዳይቀጥል እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም