ህገ ወጥ የሆኑ 19 ጠብመንጃዎችና የህክምና መድኃኒቶች የተገኘባቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

57

ጋምቤላ፤ጷጉሜን 5/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ የሆኑ 19 ጠብመንጃዎችና የተለያዩ የህክምና መድኃኒቶች ወደ መሃል ሀገር ለማሳለፍ ሲሞክሩ የተገኙ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አሰታወቀ።

በፈዴራል ፖሊስ የፈጥኖ ደራሽ የምዕራብ ዲቪዥን አንድ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሀንፍሬ ሙሐሙድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የፌዴራልና የክልሉ ፖሊስ በጋር በመሆን በጋምቤላ ከተማ ኬላ ባደረጉት ፍተሻ ነው።

በቁጥጥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ሁለቱ በተሽከርካሪ ስድስት ታጣፊና 13 ባለሰደፍ የክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች ከጋምቤላ ከተማ ወደ መሃል ሀገር ጭነው ለመውሰድ ሲሞክሩ የተገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከፍኝዶ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ የተለያዩ የህክምና መድኃኒቶች በተሽከርካሪ ጭኖ ወደ መሃል ሀገር ለማሳለፍ የሞከረ ሌላ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሂደቱ እንደተጠናቀም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት የሚላክ ይሆናል ብለዋል ምክትል ኮማንደሩ ።

የፌዴራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑም ተናግረዋል።

በተለይም አዲሱን የዘመን መለወጫ በዓል ህብረተሰቡ ያለ ምንም ስጋት እንዲያከብር አስፈላጊው ጥበቃና የክትትል ተግባራት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም