"የእኛ ትልቁ በዓላችን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ ሲደሰት ማየት ነው" -የመከላከያ ሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
"የእኛ ትልቁ በዓላችን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ ሲደሰት ማየት ነው" -የመከላከያ ሠራዊት አባላት
ጳጉሜ 5/2013(ኢዜአ) "የእኛ ትልቁ በዓላችን የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ተጠብቆ ሲደሰት ማየት ነው" ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።
ጀግኖች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ የሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት የመጨረሻ ዘቦች የመከላከያ ሠራዊት አባላት አሸባሪው ህወሓት የሚያደረገውን ወረራ ለመመከት ዛሬም ምሽግ ላይ ናቸው።
ከኢትዮጵያ ምድር ከሁሉም ጫፎች የተሰባሰቡት የመከላከያ ሠራዊት "ከራስ በፊት የህዝብን ደህንነት ማስቀደም" በሚል ጥልቅ ሀገራዊ ፍቅር ተመስርተው አዲሱን ዓመት በዱር በገደሉ ለማሳለፍ ተገደዋል።
"ሀገር ከሌለ ቤተሰብ ለምኔ" የሚሉት የኢትዮጵያ መከታዎች በአዲስ ዓመት "አዲስ የድል ብስራት እንካችሁ" ለማለት የሽብር ቡድኑን በገባበት እየገቡ ባለበት መቅበር ጀምረዋል።
የወሎ ግንባር የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሠራዊቱ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የሀገር ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ግዴታ አለበት።
በመሆኑም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትልቁ በዓሉ ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ሳይሆን "የሀገርን ሰላምና ደህንነት ጠብቆ የህዝቡን ደስታ ማየት ነው" ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ "ከራስ በፊት ለህዝብ" በሚል መርህ የተቋቋመ በመሆኑ በዓልን በምሽግ ቢያሳልፍም የህዝቡ ድጋፍና አብሮነት እንዳልተለየውም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ደጀናችን የሆነው ህዝብ "የሚያደርግልንን እንክብካቤ አሸባሪውን እስከ ወዲያኛው በመቅበር እንክሰዋለን" ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ህዝብ "እጁን ዘርግቶ አለን እንዳለን ሁሉ እኛም የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ አለኝታነታችንን እናሳያለን" ብለዋል።
ለኢትዮጵያ አንድነትና ለህዝቦች ሰላም ስንል በዓሉን በምሽግ በማሳለፍ ድል የማብሰር ጉዞ መጀመራቸውን ነው የተናገሩት የሠራዊቱ አባላት።
አዲሱን ዓመት በምሽግ ቢያሳልፉም ከጎናቸው ላልተለያቸው ደጀኑ ህዝባቸውም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሽብር ቡድኑን እየተፋለሙ ላሉ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻ አባላትም ባሉበት ቦታ ሁሉ መልካም በዓል ተመኝተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ የተለያዩ የማነቃቂያ ግጥሞችን በማቅረብ በዓሉን በምሽግ ለማሳለፍ ተዘጋጅተዋል።