''የአባይን ወንዝ ተጋሪዎቻችን ፈጣሪ የሰጠንን ጸጋ በፍትሃዊነት የመጠቀም አስፈላጊነትን ልትረዱ ይገባል''-የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ - ኢዜአ አማርኛ
''የአባይን ወንዝ ተጋሪዎቻችን ፈጣሪ የሰጠንን ጸጋ በፍትሃዊነት የመጠቀም አስፈላጊነትን ልትረዱ ይገባል''-የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ
ጳጉሜን 5፤2013 (ኢዜአ)"የአባይን ወንዝ የተፈጥሮ ጸጋ ተጋሪዎቻችን ፈጣሪ የሰጠንን ጸጋ በጋራና በፍትሃዊነት የመጠቀም አስፈላጊነትን ልትረዱ ይገባል" ሲሉ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መልእክት አስተላልፈዋል።
የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገኘት የግንባታውን ክንውን ተመልክተዋል፤ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ በሥፍራው ፀሎትና ቡራኬ አድርሰዋል።
በጉባዔው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የተነበበው የጉባዔው መግለጫ የአንድነትና ሉዓላዊነት ተምሳሌት በሆነው ግድብ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመገኘታችን ተደስተናል ብለዋል።
የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በግድቡ ያካሄዱት ጉብኝት በአዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ የተሻለ ብሩህ ተስፋ እንዲመጣ በመመኘት ጭምር መሆኑንም በመግለጫው ተመላክቷል።
በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም ተስፋን ካለመለሙ ጉዳዮች መካከል ግድቡ ለተፋሰሱ አገራት የደህንነት ስጋት ተደርጎ ጫና ለማድረግ ተሞክሮ በፀጥታው ምክር ቤት የዲፕሎማሲ ድል የተገኘበትና ሁለተኛው ዙር ሙሌትም እውን የሆነበት ተጠቃሽ መሆኑንም በመግለጫው ተጠቅሷል።
የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነት መጠቀም ከተቻለ ለሁሉም የሚበቃ መሆኑን ጠቅሰው "እኔ ብቻ ልጠቀም" የሚለው የተሳሳተ እሳቤ ግን በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም ነው ያሉት።
"ለአንተ እንዲሆንልህ የምትፈልገውን ለሌሎች አድርግላቸው" በሚለው ፍትሃዊና እኩልነት አጠቃቀም መርህ መሰረት ግድቡ በኃይማኖት አስተምህሮም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎችን የተከተለ 'እኔ ብቻ ልብላ' የሚለውን አስተሳስብ የሚጸየፍ የሰብዓዊነት ግድብ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ጉባኤው በመግለጫው "የአባይን ወንዝ የተፈጥሮ ጸጋ ተጋሪዎቻችን ፈጣሪ የሰጠንን ጸጋ በጋራና በፍትሃዊነት የመጠቀም አስፈላጊነትን ልትረዱ ይገባል" ሲል ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት መልዕክት አስተላልፏል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ልብና ሐሳብ የሚያስተሳስር የነገ ተስፋ ፕሮጀክት በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል።
"ግድቡ የጋራ ማንነት መግለጫ በመሆኑ ሁላችንም የግድቡ አምባሳደሮች መሆን አለብን" ሲል ጉባኤው በውጭ እና ሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላልፏል።