ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ጥበቃ በአስተማማኝነት ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ጥበቃ በአስተማማኝነት ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜ 5/2013(ኢዜአ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከወን የሚደረገው አስተማማኝ ጥበቃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ቀጣናውን የሚቆጣጠረው የምዕራብ ዕዝ የ22ኛ ክፍለ ጦር አስታወቀ።
የምዕራብ ዕዝ የ22ኛ ክፍለ ጦር የኦፕሬሽናል ምክትል አዛዥ ኮለኔል አዘነ ሽመልስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለምንም ስጋት ግንባታው እንዲከናወን የመከላከያ ሠራዊት ደጀን ሆኖ ቆይቷል።
"በግድቡ ዙሪያ ትንኮሳ ለማድረግ የሞከሩ ኃይሎችን የማጽዳት ሥራ ተሰርቷል" ያሉት ኮለኔል አዘነ፤ በቀጣይም የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ያለምንም ፀጥታ ስጋት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ሠራዊቱ ዋስትና እንደሆነ አረጋግጠዋል።
የ22ኛ ክፍለ ጦር ዕለት በዕለት የኢትዮጵያዊያን የዐይን ብሌን የሆነውን የኃይል ማመንጫ ግድብ እየተቆጣጠረ መሆኑን ገልጸው፤ "ምንም ዓይነት የፀጥታ ስጋት አይፈጠርም" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡን እንደ ዐይን ብሌን የሚያየው ነው" ያሉት ኮለኔል አዘነ፤ ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ሁሉ መከላከያ ሠራዊቱም ሰላምን የማረጋገጥ ተልዕኮውን ማጠናከሩን አረጋግጠዋል።
ሠራዊቱ ቦንድ ከመግዛት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡም ሲያደርግ የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
አዲሱ ዓመት የተሻለ ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸው፤ ለመከላከያ ሠራዊቱና ለኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጿል።