ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲና ዳግማዊ ሚኒሊክ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውህደት ፈጠሩ

187
አዲስ አበባ ነሃሴ 8/2010 ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲና የዳግማዊ ምኒሊክ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተዋሃዱ። በአዲስ አበባ የለውጥ እንቅስቃሴ የተቀናጀ ድጋፍ ለማበርከት በማሰብ ነው ሁለቱ ተቋማት የጋራ ስምምነት ላይ የደረሱት። የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎችና አመራሮች በተገኙበት የውህደት ስምምነት ፊርማ ዛሬ ተከናውኗል። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲውና ዳግማዊ ምኒሊክ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውህደት የፈጠሩት በሁለቱ ተቋማት ፍላጎት መሰረት ነው። ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አዲስ መዋቅር ሲያዘጋጅ የህክምና ሳይንስ የትምህርት ክፍል ማካተቱ ከዳግማዊ ምኒሊክ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር ለመስራት ምክንያት እንደሆነውም ተናግረዋል። የዳግማዊ ምኒሊክ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኩማ ጌታሁን በበኩላቸው ኮሌጁ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር ውህደት መፍጠሩ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራትና አቅሙን ለማሳደግ ያስችለዋል ብለዋል። የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብሮችን እንዲተገብር ለማድረግና ኮሌጁ የነበረበትን የአቅም ውስንነት ለማሳደግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተዋህዶ መስራቱ ወሳኝ ነውም ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በጤናው ዘርፍ የሚታዩትን የከተማዋን ችግሮችን የሚፈቱ ምርምሮችን ለማካሄድ ሁለቱ ተቋማት መዋሀዳቸው የተሻለ አማራጭ ነው። በጥናት ላይ ተመስርቶ  በአስፈጻሚ አካላት የሚደረግ የተቋማት ውህደት ለከተማው እድገትም ወሳኝ ነው ብለዋል። እስካሁን ዳግማዊ ሚኒሊክ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ  በሚል ሲጠራ የነበረውም ኮሌጁ በውህደቱ መሰረት በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የዳግማዊ ምኒሊክ ጤና ሳይንስና ህክምና ኮሌጅ የሚል ስያሜ ይኖረዋል ተብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም