ቀጥታ፡

የአሸንዳ በዓል በወዳጅነት ፓርክ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2013 (ኢዜአ) በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበረው ታሪካዊው የአሸንዳ በዓል በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ በመከበር ላይ ነው።

በበዓሉ አከባበር ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት መአዛ አሸናፊ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

በዓሉ "አሸንዳ የአንድነትና የወንድማማችነት ህያው ማስረጃ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተከበረ ያለው።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው "ኢትዮጵያ የአስደማሚ ባሕሎች መፍለቂያ ነች፤ይህንንም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይበረዝ ማሻገር ይገባል' ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው "የአሸንዳ በዓል አንድነታችንና አብሮነታችን የሚገለጽበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ሃይማኖታዊ መሰረት ያለውና አሁን አሁን ባሕላዊ ይዘቱ እያመዘነ የመጣው የአሸንዳ በዓል በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነሀሴ 16 እስከ 21 በሴቶችና በልጃገረዶች በድምቀት ይከበራል።

በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜ ያለው ሲሆን በዋግህምራ ሻደይ፣ በላስታ አሸንድዬ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በቆቦ ሶለል፣ በአክሱም ዓይነ ዋሪ እየተባለ ይጠራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም