ወጣቱ መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ መድገም አለበት-ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ መድገም አለበት-ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው
ባህር ዳር፤ ጷጉሜን 5/2013(ኢዜአ) ወጣቱ መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ በመድገም ሀገራዊ ፍቅሩን በተግባር ማሳየት እንዳለበት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አነጋግረኝ ጋሻው ተናገሩ።
ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በደብረታቦር ከተማ ከወጣቶች ጋር በተወያዩበት ወቅት ሀገርን ከተደቀነባት ችግር ማላቀቅ የሁላችንም ሀላፊነት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ከተደቀነባት ችግር የምትወጣው እንደ አፄ ቴዎሮስ በጀግንነት ወኔ በመሰለፍ አሸባሪውን ህወሓትና ተላላኪዎቹን መደምሰስ ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከተደቀነባት ውስብስብ ችግር ወጥታ ሰላምና እድገቷ እንዲረጋገጥ ህወሓትን ጨምሮ የተነሱባትን ጠላቶች በጋራ መመከትና መደምሰስ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር አነጋግረኝ ።
ወጣቱ መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ በመድገም ሀገራዊ ፍቅሩን በተግባር ማሳየት እንዳለበት አመልክተው፤ ለዚህም ወጣቶች ፈጥነው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጠይቀዋል።
በመከላከያ ሚኒስቴር የደቡብ ጎንደር ዞን ላይዘን ኦፊሰር ሻለቃ ሙሉ አዳነ እንዳሉት፤ ተተኪ ጄነራልና የነገ ጦር መሪ ለመሆን ዛሬ ወታደር መሆንን ይጠይቃል።
የኢንጅነሪንግ፣ የህክምናና ሌሎች የረቀቁ ሳይንሳዊ ወታደራዊ ስልጠናዎችን በመውሰድ ሀገርን ማገልገልና ራስንም መጥቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።
የደብረ ታቦርና አካባቢው ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀልና አሸባሪውን ህወሓት በመደምሰስ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲያሳይም ሻለቃ ሙሉ ተናግረዋል።
''መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል ሀገርንና ህዝብን ከወራሪ ኃይል መታደግ ነው'' ያሉት ደግሞ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንዴ መሰረት ናቸው።
ወጣቱ ይህንን በጎ ተግባር ሲያደርግ አሁን በአሸባሪው ህወሓትና ሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ በድል መወጣትና ሀገርን ከብተና ማዳን ይችላል ብለዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣት መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል ራሱንም ሆነ ሀገሩን ከወራሪ ጠላት እንዲጠብቅም ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል።
መከላከያን ለመቀላቀል መመዝገቡን የገለጸው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ ወጣት አምሳሉ አይናለም፤ አሸባሪው ህወሓት ንጹሀንን ሲገድልንና ሲያሳድድ ማየቱን ለመመዝገቡ ምክንያት እንደሆነው ተናግሯል።
አሸባሪው ህወሓት የሚጠፋበት ጊዜ አጭር ነው ያለው ወጣት አምሳሉ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ሀይሎችን ለመከላከል ወታደራዊ ስልጠና መውሰድና ሠራዊቱን መቀላቀል ግዴታ መሆኑን አስታውቋል።
ወጣቶች ሰልጥነን ሀገራችንንና ወገኖቻችንን ካልጠበቅን የእኛም ህልውና አደጋ ላይ እንደሚሆን በመረዳት መከላከያ ሠራዊትን ከወዲሁ መቀላቀል ይገባል ብሏል ወጣት አምሳሉ።
''መከላከያን በመቀላቀል እንደነ አፄ ምኒልክ እና አፄ ቴዎድሮስ ሀገሬን ከጠላት ለመጠበቅ ተዘጋጅቻለሁ'' ያለው ደግሞ ወጣት አየነው ታረቀኝ ነው ።
አሸባሪው ህወሓት ወሯቸው በነበሩ አካባቢዎች የወገኖቹን ሃብት እየዘረፈ ሲሄድ መመልከቱ ሰራዊቱን በፈቃደኝነት ለመቀላቀል እንዳነሳሳው ተናግሯል።
በወቅታዊ የማነቃቂያ ፕሮግራምና የውይይት መድረክ ላይ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር አመራርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።