ቀጥታ፡

አዲሱ አመት ከድጋፍ ጠባቂነት የምንላቀቅበት ይሆናል

ክልል ጳጉሜ 5 /2013 (ኢዜአ) አዲሱ አመት ህዝባዊ እሴቶቻችንን በተጨባጭ የምናሳይበትና ከድጋፍ ጠባቂነት የምንላቀቅበት ይሆናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

ርእሰ መሰተዳደሩ አዲሱን ዓመት በማስመልከት የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

ርእሰ መሰተዳደሩ በመግለጫቸው  "በ2013 አመት በርካታ ፈተናዎችን አስተናግደናል፣ ይሁን እንጂ በተባበረ ክንድ ፈተናዎቹን ተቋቁመን ድርብ ድል አስመዝግበናል" ብለዋል። 

"ይፈርሳሉ ስንባል እየተገነባን፣ይጫረሳሉ ስንባል አንዱ ለሌላው መከታ ሆነን በችግር ውስጥ አንድነታችንን አጠናክረን በጠላቶቻችን ላይ ድል እየተጎናፀፍን እንገኛለን" ሲሉም አመልክተዋል።

"የህዝባችንን ጥቅም ለማስከበር በመስራት ላይ እንገኛለን" ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ  "የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን የመወሰን ነፃነት በማረጋገጥ ላይ እንገኛለን" ሲሉም ተናግረዋል።

"ያለንበት ታሪካዊ ምዕራፍ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በእጅ አዙር በአገራችን ላይ ሲቃጣ የነበረውን ሴራ በግልፅ ያሳየና የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝቦችን ነፃነት ለመጠበቅ ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈልን ነው " ብለዋል።

2013 ዓ.ም በበርካታ ፈተናዎች ተከበን ያስመዘገብነው ድርብ ድል የአመራሩና የህዝባችን ተደማምጦ የመስራት ውጤት ነው " ብለዋል ።

በክልሉ በ2013 ዓ.ም ከ11ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው በደ ስራ የገቡበት ና በመሰኖ ልማት ዘርፍ አበረታች ወጤት የተመዘገበበት መሆኑን ለአብነት ጠቁመው በ2014 አመትም የተጀመሩ የልማት ሰራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት እንደሚሆን አመላክተዋል ።

በአዲሱ አመት የግብርና ቴክኖሊጂ አቅርቦትን በመጨመር የኩታ ገጠም አስተራረስን ከማጠናከር ጎን ለጎን ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር ግብርና የሚረጋገጥበት እንደሚሆንም አስታውቀዋል ።

"የአገር ውስጥ ምርቶችን በእጥፍ በመጨመር የኑሮ ውድነትን  ለማቃለል የምንሰራበት ዘመን ይሆናል" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ  የአረንጓዴ አሻራ ስራችንን ወደ ልዩ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት ይሆናል ሲሉም አመልክተዋል ።

"ዛሬ የ2014 ዓ.ም ዋዜማ በዓል ስናከብር ለማይክሮ ሰከንድም ቢሆን የአገራችንን ሰላም ከመጠበቅ ልንዘናጋ አይገባም" ያሉት ርአሰ መስተዳደሩ " ሀሳባችንና ስሜታችን ሁሉ የአገራችንና ህዝባችንን ሰላም መጠበቅ ላይ መሆን አለበት" ሲሉም አስገንዝበዋል ።

በዚህ አጋጣሚ ታሪካችሁን በደማቅ ቀለም ላሸበረቃችሁ ለአገር መከላከል ሰራዊት፣ ለመደበኛ ፖሊስ፣ ለልዩ ሀይልና ለፌደራልና ክልል ፀጥታ አካላት እንኳን ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁ ስል ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል" ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

"ለአገር ሉዓላዊነትና ለህዝባችሁ ነፃነት እየከፈላችሁ ባለው መስዋዕትነት አኩሪ ድል አስመዝግባችኋል፣ ዛሬም እያስመዘገባችሁ ትገኛላችሁ " ብለዋል።

"እኛም ለሰጣችሁን አደራ ታማኝ ሆነን ባለንበት ቦታ ሁሉ ከቤተሰቦቻችሁና ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር ማዕድ ለመካፈል ወስነናል " ሲሉ በመግለጫቸው አመልክተዋል ።

ርእሰ መሰተዳደሩ አዲሱ አመት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ  የሰላምና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም