የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ሠላም እስከሚያገኝ ግዳጃችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ሠላም እስከሚያገኝ ግዳጃችንን እንወጣለን
ጳጉሜን 5/2013 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ሠላም እስከሚረጋገጥ ድረስ ግዳጃችንን በሚገባ እንወጣለን ሲሉ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።
አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራቸው አካባቢዎች አስከፊ ኢ-ሠብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል።
የሽብር ቡድኑ ንጹሃንን ገድሏል፣ ሴቶችን በቡድን ደፍሯል፣ እንስሳትን አርዶ በልቷል፣ ከሊጥ እስከ ጓሮ እህል ዘርፏል መውሰድ ያልቻለውንም አውድሟል።
የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻዎችም ይህ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት በገባበት ቦታ ሁሉ እየደመሰሱት ይገኛሉ።
የወሎ ግንባር የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሽብር ቡድኑና አስተሳሰቡ ከኢትዮጵያ ምድር እስኪጠፉ ድረስ የህልውና ዘመቻው ይቀጥላል ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተማማኝ ሠላምና ደህንነት እስከሚያገኝ ድረስም ግዳጃቸውን በብቃት ለመወጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የሕዝቡን ደጀንነት ተጠቅመን የተጣለብንን ኢትዮጵያን የመጠበቅ አደራና ሃላፊነት በድል እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ከአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሺያና ከመላው ሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ የሽብር ቡድኑን ድባቅ እየመታ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውን ሁሌም አሸናፊዎች ናቸው የሚሉት የሠራዊቱ አባላት በሽብር ቡድኑ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ይቀጥላል ብለዋል።
በቅርቡም የሽብር ቡድኑ ከአማራና አፋር ክልሎች ተጠራርጎ ወጥቶ ሕዝቡ በቀዬው የሠላም አየር መተንፈስ ይጀምራል ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ ከወረራቸው የአማራና የአፋር ክልሎች እየተደመሰሰ የቀረውም እግሬ አውጪኝ ብሎ እየሸሸ መሆኑ ይታወቃል።