ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም

91

ጊዜ በረርክ በረርክ

ጊዜ በረርክ በረርክ

ግና ምን አተረፍክ

ግና ምን አጎደልክ?

ሞትን አላሸነፍክ

ሕይወትን አልገደልክ።

ሲል ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ የተቀኘው ያለምክንያት አልነበረም ዘመን እየዞረ በመጣ ቁጥር ህያዋን እየተወለዱ ማደጋቸው ቀጥሎም መሞታቸው ከዚያም መረሳታቸው አስገርሞት እንጂ።

እንደባለቅኔው ጊዜንና ጊዜን እየታከኩ የሚመጡ ሁነቶችን የሚታዘብ ሁሉ ከራሱ ከቤተሰቡ ከአካባቢው ብሎም ከአገሩና ከአለም ጋር የተያያዙ ክፉም ሆኑ መጥፎ ትዝታዎች እንደሚመጡበት እሙን ነው።

ኢትዮጵያም አዲስ ብላ የተቀበለችውን 2013 ዓ.ም ከውስጣዊና ውጫዊ ተጽእኖዎች፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ውጥረት፣ ከስራ አጥነት፣ ካለመረጋጋትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተደማምሮ እንዴት ያልፋል በሚል ብዙዎች በተስፋና ስጋት መካከል እንዳሳለፉ ግልጽ ነበር።

በ2012 ዓ.ም በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ከተላለፈ በኋላ፤ በትግራይ በተናጠል የተካሄደው ክልላዊ ምርጫ ሕገ-ወጥና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ቢያሳልፍም ተግባራዊ ሳይደረግ በዛው አመት ወርሃ ጳጉሜ ክልላዊ ምርጫው ተካሄደ ተባለ።

በህገወጥ መንገድ የተካሄደው ምርጫ መራጮች ከጠዋት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፃቸውን ሲሰጡ መዋላቸውን አሸባሪው ህወሃት የሚመራቸው ድምጸ ወያኔና ትግራይ ቴሌቪዥን የዘገቡ ሲሆን ዘግይቶም ክልሉን ሲመራ የነበረው ሽፍታ ቡድን በሰፊ የድምጽ ብልጫ ማሸነፉን ካስነገረ ከቀናት በኋላ ዘመን ተለውጦ 2013 ዓ. ም ገባ ።

ኢትዮጵያውያን ከመስከረም አንድ የበአል ድባብ ሳይወጡ በመጀመሪያው ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለብዙዎቹ ድንገተኛ የሆነውን የገንዘብ ኖቶች ቅያሬ ይፋ ሲያደርጉ ብሄራዊ ባንክ ቀደም ሲል ካወጣቸው አዳዲስ ገንዘብ ነክ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ ጥርጣሬው የነበራቸው አካላት ተከታታይ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ምላሽ እየተሰጠ የገንዘብ ለውጡ ከሶስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።

በርካቶች በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተራዘመበት መንገድ ህግና ህጋዊነትን የተከተለ መሆኑን ቢናገሩም የራሱን ምርጫ አድርጎ ትግራይን በእጁ ማስገባቱንና ክልሉን የሚመራ መንግስት መመስረቱን የተናገረው አሸባሪው ህወሃት ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግስት የለም የሚሉ ሀይሎችን ከአገር ውስጥና ከውጪ በማሰባሰብ ጩኸቱን እንዲያደምቁለት ለማድረግ ሞክሯል።

መንግስት በበኩሉ በትግራይ ተደርጓል የተባለው ምርጫ ህገ-መንግስቱን የጣሰ በመሆኑ ተመስርቷል ከተባለው የክልሉ መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደማይኖረው ግልጽ በማድረግ አስፈላጊ የስራ ግንኙነቶች ከቀበሌና ከወረዳ መዋቅሮች ጋር ብቻ እንደሚሆኑ እወቁት አለ።

አሸባሪው ህወሃት ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት እንዲያስችለው ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም በማለት በዜጎች ላይ ፍርሃት ለመንዛት ተከታታይና የተቀናጁ ብጥብጥ የመፍጠር ሙከራዎችን ቢያደርግም የተባለው ቀን አልፎ ወርሃ ጥቅምት እንዳመጣጡ ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ሲቀረው በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ያልተጠበቀ ጨካኝና ነውረኛ ጥቃት ፈጸመ።

ጠቅላይ ሚንኒስትር ዐብይ አህመድ በአሸባሪው ህወሓት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ወታደራዊ እርምጃ ተወስዶ ህግ የማስከበር ዘመቻው ተግባራዊ እንዲሆን መከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስን ያዘዙ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ኅዳር 19 የመከላከያ ሠራዊት መቀሌን ተቆጣጥሯል።

ቀጣዩ ተግባር በሕግ የሚፈለጉ የቡድኑ አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋልና ትግራይን መልሶ መገንባት መሆኑ ተገልጾ፤ ከፍተኛ የቡድኑ አመራሮች በመከላከያ ቁጥጥር ስር ሲውሉ የተወሰኑት ደግሞ ተደምስሰዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ በአጣዬና አካባቢው የሸኔ ቡድን አባላት በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ጥቃት በማድረስ በርካታ ሰዎችን የገደሉ፣ ዝርፊያ የፈጸሙና ከተማዋን ያወደሙ መሆናቸው ተሰማ።

በአካባቢው ጥቃት የሰነዘሩትን የሸኔ ታጣቂዎች ለመከላከል የአማራ ልዩ ኃይልና የአገር መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ገብተው ሰላም የማስፈን እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን አሸባሪዎቹ ሸኔና ህወሃት አብረው እየሰሩ ሰላም እያደፈረሱ መሆኑን መንግስት የገለጸውም በዛ ወቅት ነበር።

በትግራይና በአማራ ክልሎች ያለው ሁኔታ እንደዚህ በመሆኑ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደሚስተጓጎል ተስፋ በማድረግ ሰፊ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ዘመቻ ውስጥ የከረሙት የሱዳንና የግብጽ ባለስልጣናት ከአፍሪካ ህብረት አሜሪካ ብሎም ወደ አውሮፓ ህብረት፣ የአረብ ሊግና የጸጥታው ምክር ቤቶች እየተወረወሩ ኢትዮጵያን ትንፋሽ ለማሳጣት ያደረጉት ሙከራ እንዳሰቡት መሳካት አልቻለም።

የሕዳሴ ግድብ 10ኛ ዓመትን በማስመልከት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በግድቡ ድርድር ላይ የተሳተፉ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን በተለያዩ መንገዶች አስተያየታቸው ሲሰጡ የሰነበቱ ሲሆን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በቀጣዩ ክረምት ቀጠሮ የተያዘለት 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘምና ለዚያ የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለና የግድቡ ግንባታም ከ80 በመቶ መሻገሩን እወቁት አሉ፡፡

ግብፅና ሱዳን አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት መከናወን እንደሌለበት ከመወትወት አልፈው ወታደራዊ የትብብር ስምምነት በማድረግና ልምምዳቸውን በማሳየት ኢትዮጵያን ለማስፈራት ከመሞከራቸውም በላይ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ተመድ በአደራዳሪነት እንዲሳተፉና የውሃ ሙሌቱን ዓለም ዓቀፋዊ አጀንዳ ለማድረግ በብዙ መትጋታቸው ይታወሳል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ሰብሳቢ የነበሩት የፈረንሳይ አምባሳደር ኖኮላስ ደ ሪቪዬር የጸጥታው ምክር ቤት የሚያደርገው ስብሰባ ጉዳዩን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እንደማይኖረው አስቀድመው ቢናገሩም ሁለቱ አገራትና አጋራቸው የአረብ ሊግ ባደረጉት ተማጽኖ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ለስብሰባ መቀመጡ አልቀረም ነበር።

ምክር ቤቱ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሶስቱ አገራት በሚያደርጓቸው ውይይቶች ይፈታ የሚል ሃሳብ ከማቅረቡም በላይ አሳሪ የሆነ ስምምነት ሳይደረግ የውሃ ሙሊቱ እንዳይጀመር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ኢትዮጵያ በዕቅዷ መሰረት ውሃ መሙላቱን መጀመሯን ለሱዳንና ለግብፅ ባለሥልጣናት ካሳወቀች በጥቂት ሳምንታት በኋላ ግድቡ ሞልቶ ሲፈስ አለም መመልከት ቻለ።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ ስትነሳ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የጸጥታ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ስላጋጠሟት ምርጫውንም ለማራዘም ተገዳ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሲሆን ጸረ ኢትዮጵያ አቋማቸውን በግልጽም ሆነ በድብቅ ሲያንጸባርቁ የነበሩ አካላት ከምርጫው በኋላ ብጥብጥ ለመፍጠር የሚያግዟቸውን ቅድመ ዝግጅቶች ከወዲሁ በማጠናቀቅ ውጤት እስኪነገር በጉጉት ሲጠባበቁ ከርመዋል።

በምርጫው እለት ማምሻውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት መግለጫ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ይሄ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠመ፤ ሰላማዊነቱ ተረጋግጦ የተከናወነ ስለመሆኑ አንስተው መራጩ ህዝብ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በቁርጠኝነት ድምጹን ስለሰጠ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በምርጫውም ኢትዮጵያ አሸንፋበታለች።

የአሜሪካና አጋሮቿን ቡራኬ ባላገኘው ምርጫ የተሳተፉ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ምርጫው የሚሻሻሉ ጉዳዮች ቢኖሩትም በአንጻራዊነት ሰላማዊና አሳታፊ እንደነበር በመግለጽ የፖለቲካ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉና ያሉባቸውን ክፍተቶች በማስተካከል ለሚቀጥለው ምርጫ እንደሚዘጋጁ በመግለጽ የታሰበው ሁከትና ብጥብጥ እቅድ እንዳይሳካ በማድረግ በኩል ድርሻቸው የጎላ ነበር።

ነገሮች በዚህ መንገድ እየሄዱ ባለበት ወቅት በትግራይ ያለው አርሶ አደር “ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲከውን” እንዲሁም “የእርዳታ ስራው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሰራጭ” በማሰብ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ እርሻ ወቅት ማጠናቀቂያ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ይፋ ሆነ።

በውሳኔው መሰረትም ሁሉም የፌዴራል እና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ማዘዙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

“በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ” የተኩስ አቁም ላይ የተደረሰው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ “ሰላምን የሚመርጡ የሕወሓት አባላት “እንደገና ለማሰብና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ዕድል እንዲያገኙና በትግራይ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ወዳጆች ሲቀርቡ የነበሩ የመፍትሔ ሃሳቦችን የፌዴራል መንግስት ሲያጤናቸው በመቆየቱ መሆኑም ተገልጿል።

የአሸባሪው ድርጅት መሪዎች መከላከያ ሙሉ ለሙሉ ለቆ መውጣቱን ባረጋገጡ ማግስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ሲሰሩ የነበሩ ንጹሃንን በህዝብ ፊት በመግደል ጭካኔያቸውን በማሳየት በክልሉ ያሉ ወጣቶችና ለጋ ህጻናት ያለምንም ጥያቄ ድርጅቱን ተቀላቅለው የጥፋቱ አካል እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ድርጅቱ ከአገር ባሸሸው በርካታ ቢሊዮን ዶላር አማካይነት የአውሮፓና የአሜሪካ ባለስልጣናትን መወትወት የሚችሉ ኩባንያዎችን ግለሰቦችንና የሚዲያ ተቋማት መሪዎችንና ጋዜጠኞችን አቀናጅቶ በማሰማራት ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መመራቱና መወያያ መሆኑ ይታወቃል።

ስብሰባው ኢትዮጵያ በክፉ ጊዜ ወዳጅ የሆኗትንና መውደቋን በጉጉት የሚጠባበቁ አካላትን እንድትለይ መልካም አጋጣሚ ስለመፍጠሩ በርካቶች የተስማሙበት ሲሆን ኢትዮጵያውያንም ከያሉበት ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ባደረጉት ተሳትፎ የአገራቸውን እውነት አለም እንዲያውቀው ጥረዋል።

የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን መተው የተሻለ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ከሞገቱት አገራት ተወካዮች ባሻገር የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው በጦርነቱ የሚሣተፉ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የተማጸኑ ሲሆን በድርጅቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ሁኔታ ልወስን የሚሉ የውጭ ኃይሎች ተቀባይነት እንደሌላቸው አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል።

ለሰላም አማራጭ እድል መስጠት ያልፈለገው አሸባሪው ህወሃት የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ መውጣቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ በአጎራባች የአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ባደረሰው መጠነ ሰፊ ወረራ በርካቶች ሲገደሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ነፍሳቸውን ለማዳን የመኖሪያ አካባቢያቸውንና ሃብት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ ዘረፋና ንብረት ማውደም ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል።

የድርጅቱ ጥፋት ከዚህ በላይ እንዲዘልቅ ያልፈቀዱ ኢትዮጵያውያንም በብዛት መከላከያን በመቀላቀልና በየአካባቢያቸው ራሳቸውን በማደራጀት ለመከላከያ ሰራዊት ለልዩ ሃይሎች፣ ለፖሊስ፣ ለሚሊሻና ለአካባቢ ታጣቂዎች እገዛ በማድረግ አሸባሪውን ከያዛቸው ከተሞች አስወጥተው አስፈላጊውን ቅጣት በመስጠትና ለላኩት አካላት መልእክት በማስተላለፍ ወደመጣበት በመሸኘት ላይ ይገኛሉ።

የመንግስት ሃይሎች በህዝብ ደጀንነት የአገር ውስጥና የውጭ የሽብር ግብረ አበሮቹን አሰባስቦ ጉዳት እያደረሰ ያለው ድርጅቱ ዳግም ህልውና እንዳይኖረው የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ እየተደረጉ ባሉ ዘመቻዎችም በርካታ የድርጅቱ አላማ ፈጻሚዎች ሙትና ቁስለኛና  ሲሆኑ ጥቂት እድለኞች ደግሞ ምርኮኞች ሆነዋል።

ከሞላ ጎደል በሚበረው ጊዜ ውስጥ አመቱን በዚህ ሁኔታ ያሳለፈችው ኢትዮጵያ መጭውን አዲስ አመት ነቀርሳ የሆኑባትን የአገር ውስጥ በሽታዎች በማስወገድና የተሻሉ ስኬቶችን በማምጣት እንደምታከብረው ተስፋ ተሰንቋል።

ኢትዮጵያውያን አዲስ አመትን የምናከብርበት ወርሃ መስከረም እድሜ የሚጨምርበት፣ ከጭለማ ወደ ብርሃን፣ ከመከፋት ወደ ደስታ መሸጋገሪያ ድልድይ ትላንትን በትዝታ ዛሬን በስራ ነገን ደግሞ በተስፋ የምናይበት ማማ በመሆኑ አዲሱ አመት ለሃገራችን ሁለንተናዊ ስኬት የሚያጎናጽፍ እንዲሆን እየተመኘን በሚበረው ጊዜ ላይ ተሳፍረን ጥቂት በማጉደል ብዙ ለማትረፍ ለማሸነፍና ካቀድነው ለመድረስ እንጣር ። መልካም አዲስ አመት !!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም