አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሽልማት ተበረከተላቸው - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሽልማት ተበረከተላቸው
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5/2013 (ኢዜአ) አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ የ2020 የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የእውቅና ሽልማት ተበረከተላቸው።
አምባሳደር ቆንጂት ሽልማቱን አዲስ አበባ በሚገኘው የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት በተካሄደው መርኃ ግብር በአፍሪካ ህብረት የጃፓን ቋሚ መልዕክተኛ ከአምባሳደር ኦሪ ዮቺ ቶሺሂኮ ተቀብለዋል።
ሽልማቱ አምባሳደር ቆንጂት በጃፓንና በአፍሪካ መካከል የጋራ መግባባት እንዲኖር ላደረጉት የላቀ አስተዋፅዖ እንደተበረከተላቸው ተገልጿል።
እንዲሁም ሽልማቱ አምባሳደሯ በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በነበሩበት ወቅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በጃፓን ዮካሃማ በተካሄደው አምስተኛው የጃፓን አፍሪካ የልማት ፎረም(ቲካድ) ውጤታማ እንዲሆን ለነበራቸውም አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠ ነው ተብሏል።
አምባሳደር ቆንጂት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1954 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከለንደን ኮሌጅ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች አግኝተዋል፤ ቀጥሎም የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ነበሩ።
አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በለጋ ዕድሜያቸው ተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት አገልግለዋል።
አምባሳደሯ በካናዳ ኦታዋ፣ በግብጽ ካይሮ፣ በእስራኤል ቴል አቪቭና በኦስትሪያ ቬና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ሥምምነት ላይም ልዩ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።
አምባሳደር ቆንጂት ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ አገልግለዋል፤ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር ናቸው።
አምባሳደር ቆንጂት በዲፕሎማሲው መስክ ለነበራቸው አበርክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም የእውቅና ሽልማት ሰጥቷቸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት እውቅና የሰጣቸው ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።
የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ሆርዶፋ በቀለ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ የጃፓን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሽልማት ሰጥቷቸዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ንዋይ ገብረ አብና ዶክተር አርከበ እቁባይ የክብር ኒሻን ሽልማት እንደተበረከተላቸው ይታወሳል።
በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና የመንግሥት የአፍሪካ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።