ቀጥታ፡

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለአቅመ ደካሞችና የስጋ ደዌ ህሙማን የበዓል ስጦታ አበረከቱ

ጷጉሜ 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞችና የስጋ ደዌ ህሙማን የበዓል ስጦታ አበረከቱ።

ቀዳማዊት እመቤቷ በአዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል አካባቢ የሚኖሩ አቅመ ደካሞችንና የስጋ ደዌ ህሙማንን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት "እንኳን አደረሳችሁ" በማለት የበግና ሌሎች የተለያዩ ስጦታዎች ለግሰዋል።

በተመሳሳይም ለ100 የስጋ ደዌ ህሙማን ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሺህ ብርና ብርድ ልብስ ስጦታ አበርክተዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ እንደገለጹት፤ አዲሱ ዓመት ሲከበር እረዳት የሌላቸውና የተረሱ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማስታወስ ሊሆን ይገባል።

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ የሚደጋገፉበት፣ የሰላም፣ የአንድነት የፍቅር እንዲሆንም ተመኝተዋል።

ኢትዮጵያውያን መጪውን አዲስ ዓመት ሲያከብሩ የተቸገሩና ረዳት የሌላቸው ወገኖች በመርዳት እንዲሆንም ጠይቀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የአንድነት፣ የይቅርታና የመደጋገፍ እንዲሆን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው አቅመ ደካሞችና የስጋ ደዌ ህሙማን ቀዳማዊት እመቤት ላደረጉት ድጋፍ በማመስገን በዓሉን በደስታ እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል።

በተለይም ስለስጋ ደዌ ህመም በማህበረሰቡ ዘንድ ባለው የግንዛቤ እጥረት ምክንያት የሚደርስባቸውን መገለል በማንሳት ቀዳማዊት እመቤት ያደረጉት ጉብኝት በአርአያነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም