የመተከል ግጭት በአዲሱ አመት አይቀጥልም - ኢዜአ አማርኛ
የመተከል ግጭት በአዲሱ አመት አይቀጥልም
አሶሳ ጳጉሜ 05 / 2013 ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለዓመታት የዘለቀው ግጭት በአዲሱ አመት አይቀጥልም ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስታወቁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የዘመን መለወጫን በዓልን በማስመልከት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል ።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በመግለጫቸው እንዳሉት 2013 ዓመት ኢትዮጵያዊያን አሸባሪው ህወሃት በደቀነው ፈተና ውስጥ ሆነው ውጤት ያስመዘገቡበት ዓመት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ያሸነፉበትን ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ፣ ሁለተኛው ዙር የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌትና የሶስተኛውን ሃገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ውጤቶችን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
"2013 ዓመት ኢትዮጵያዊያን ፈተናን ወደ ስኬት የመቀየር የአባቶቻችንን ታሪክ የደገምንበት ነው "ብለዋል።
በተለይም የአሸባሪው ህወሃት ርዝራዦች በክልሉ መተክልና ካማሽ ዞኖች ለዓመታት ባስከተሉት ግጭት የጠፋውን የሰው ሕይወትና ንብረት አስታውሰው የክልሉ መንግስት ከዞኑ ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱንአመልክተዋል፡፡
"ይሁንና የጥፋት ቡድኑ ርዝራዦች የአካባቢው ግጭት እንዳይቆም የማድረግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል" ብለዋል።
አጥፊዎቹ አካባቢውን ዋነኛ ትኩረት ያደረጉት ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በዞኖቹ ያለው ማዕድንና ለም መሬት እንዳይለማ ለማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት በመተከልና ካማሽ ዘኖች ግጭት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል የክልሉ መንግስት ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በመቀናጀት በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
የግጭቱ ተፈናቃዮችን መልሶ በዘላቂነት የማቋቋምና የተጎዱ አካባቢዎችን የመገንባት ስራዎችም የአዲሱ አመት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አመላክተዋል።
"የጥፋት ቡድኑ በዜጎች ላይ ሰብዓዊ ጉዳት እያደረሰ የሚቀጥልበት ምክንያት አይኖርም" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም ግጭን በዘላቂነት ለመፍታት ውስጣዊ ችግሮችን ለማጽዳት ላይ ትኩረት ያደረገ ሁለንተናዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የህወሃት ሽብር ቡድን የጥፋት ተላላኪዎችን ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ተደራጅቶ እንዲታገል ጠይቀዋል፡፡
ለመላው ኢትዮያዊያን አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የልማትና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡