ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ የመከራ ጊዜዋን አልፋ የድል ብስራት የምትሰማበት ዓመት እንደሚሆን ተስፋችን ነው--- ዲያስፖራዎች

አዲስ አበባ  ጻግሜ 5/2013 (ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ የመከራ ጊዜዋን አልፋ የድል ብስራት የምትሰማበት ዓመት እንደሚሆን ኢዜአ ያነጋገራቸው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እምነታቸውን ገለጹ።

ኢትዮጵያውያን አዲሱን የ2014 ዓመት ለመቀበል እንሆ ሰዓታት ቀርተዋቸዋል።

አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው ዳያስፖራዎች  እንደሚሉት ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም በችግርና በመከራ ውስጥ ያለፍበት ፈታኝ ጊዜ ነበር።

ልንሰናበተው እየተዘጋጀነው ባለው ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮች በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያስጨነቀ እንደነበረም ነው የተናገሩት።

በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች ተፈትናለች፤ 2014 ዓ.ም ግን ኢትዮጵያ ያለችበትን አስጨናቂ ጊዜ በማለፍ ድሏን የምታረግጥበት ዓመት ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ዳያስፖራዎቹ ገልጸዋል።

"አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ጠላቶች አንገታቸውን ይደፋሉ፤ሕዝቡ በምርጫ የመረጠው አዲስ መንግስት ተመስርቶ አዲስ ስርዓት የሚገነባበት ዓመት በመሆን አገራችን ትልቅ ተስፋ አላት" ነው ያሉት ።

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የሚታያቸው ተስፋና ብርሃን መሆኑንም ተናግረዋል። 

አዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ ከጦርነትና ችግር ወጥታ ሕዝቦቿ በሰላምና በፍቅር የሚኖርበት ዓመት ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ትነሳለች፤ ኢትዮጵያ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሻገሩ ጥርጥር የለንም ነው ያሉት ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ።

ዳያስፖራው በ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ በሚያሻሽሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

2014 የኢትዮጵያ የምስራች የሚበሰርበት ጠላቶች አንገታቸው የሚሰበርበት እንደሚሆን በእንግሊዝ አገር የሚኖሩት አቶ አለባቸው ታደሰ  ይገልጻሉ።

 በአሁኑ ሰዓት ዲያስፖራው የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ ህዝቡ ህዝብ በፍቅር ተያይዞ እንደምናሻገረው አምናለሁ የሚሉት ደግሞበኖርዌይ አገር የሚኖሩት ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ ናቸው።

አቶ ዘውዴ መንግስቱ "አገራችን በሰላምና በፍቅር በአንድነት እንድትኖር በተለይም ጦርነት የሚባል ነገር ከሀገራችን ምድር ጠፍቶ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሚኖርበት እና በሚሰራበት ሰላም አግኝቶ እንዲሰራ የሁላችንም ተስፋ ነው። " ብለዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 2014 ዓ.ም ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሰላም፣የፍቅር፣የደስታ ፣የነጻነትና የድል ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ያላቸውን በማካፈል መልካምነታቸውን ሊያሳዩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም