ቀጥታ፡

የተፈናቃዮቹ የአዲስ ዓመት ተስፋ

አዲስ አበባ ዻጉሜን 05 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአዲአርቃይ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ መቅደስ የማታ አውደ ዓመትን በሞቀ ጎጆዋ፤ ከቤተሰቦቿና ጎረቤቶቿ ጋር በደስታ ስታከብር ነው የኖረችው፤ ዛሬ ግን 'ተፈናቃይ' ሆና በመጠለያ ጣቢያ ትገኛለች፤ ምክንያቱ ደግሞ የአሸባሪው የህወሓት ወረራ፣ ግፍና በደል ነው።
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ፣ ጠለምት እና ደባርቅ ዙርያ ቀበሌ በርካታ ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው ደባርቅ ከተማ ይገኛሉ።

እነዚህ ዜጎች ወትሮ ዓውደ ዓመትን በኢትዮጵያዊ ወግና በባህል ከቤተሰብና ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሞቀ ቤታቸው በደስታ የሚያሳልፉ ነበሩ።

ይሁንና አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ማፍረስ በሚል ህልም በከፈተው ጦርነት ሳቢያ የ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ለማሳለፍ ተገደዋል።

ኢዜአ ተፈናቃዮቹ አዲሱን ዓመት እንዴት እንደሚያከብሩ፣ የዘመኑ ተስፋቸው ምን እንደሆነ ጠይቋቸዋል።

የአዲአርቃይ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ መቅደስ የማታ የአሸባሪው የህወሓት ቡድን በአካባቢው እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ሸሽታ መምጣቷን ትናገራለች።

አሸባሪው ቡድን አካባቢውን ከመውረሩ በፊት "የተሻለ ሕይወት ነበረኝ" ያለችው ወይዘሮ መቅደስ "አሁን ተፈናቃይ ሆኜ የሰው እጅ እየጠበኩኝ እገኛለሁ" ስትል በሃዘን ስሜት ተናግራለች።
ይሁንና "በአሸባሪው ህወሓት ተፈናቅለን በዓሉን ከጎረቤቶቻችን ጋር ሳይሆን ከቤታችን ውጭ ለማክበር ብንገደድም ሁሉም አገራችን ስለሆነ አዲስ ዓመትን ከደባርቅ ሕዝብ ጋር እናከብራለን" ብላለች።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአጭር ጊዜ ተደምስሶ ወደ ቀደመው ሕይወታቸው ተመልሰው የሠላም ኑሯቸውን እንደሚቀጥሉም ተስፋዋን ገልጻለች።

"በአዲአርቃይ እያለሁ የተሻለ ኑሮ ነበረኝ ይሁን እንጂ አሸባሪው ቡድን በከፈተብን ጦርነት ከቤተሰቦቼ ጋር ተፈናቅዬ የሰው እጅ እንድንጠብቅ ሆኛለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ መሐመድ ኑርአደም ናቸው።

እርሳቸውም ወራሪው ቡድን ተደምስሶ ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሠላማዊ ኑሯቸውን እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

አቶ መሀመድ "አሸባሪውን ቡድን ደምስሰን የኢትዮጵያ ሕዝብ በየአካባቢው ነፃነቱን አግኝቶ እንዲኖር ማድረግ አለብን" ብለዋል።

ወይዘሮ ስመኝ ጌታቸው እና ቦሰኗ ሀጎስም በዓልን እንደአቅማችን በማዘጋጀት እንውል ነበር አሸባሪው ቡድን አፈናቅሎን ከሞቀ ጎጇችን ወጥተን በስደት እያሳለፍን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በአሸባሪው የህወሓት ላይ እየወሰዱት ባለው እርምጃ ቡድኑ ተደምስሶ በአጭር ጊዜ ወደ አካባቢያቸው እንደሚመለሱ ተፈናቃዮቹ ተስፋ ሰንቀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሰርጎ በገባባቸው የሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ፣ ጠለምትና ደባርቅ ዙሪያ ቀበሌዎች ከ75 ሺህ በላይ ዜጎችን አፈናቅሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም