የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ ሁለት ተርባይኖች በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ
ዻጉሜን 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወራት ሃይል ማመንጨት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
ኢዜአ በግድቡ ግንባታ ስፍራ በመገኘት ከሚኒስትሩ ጋር ባደረገው ቆይታ በ2013 ዓ.ም በድርድሩ የተለያዩ ፈተናዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ሆኖም የግድቡ ግንባታ በአስቸጋሪው ጊዜም ተጠናክሮ በመቀጠሉ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወራት የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ብለዋል።
በዚህም ቀሪ ስራዎች በጥቂት ጊዜያት አጠናቀው በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ ወራት ላይ ሃይል ማመንጨት እንዲችል ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣሪ የሰጣት ጸጋዋን የመጠቀም መብት አላት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከምፅዋትና ድህነት መውጣት የሚቻለው ጠንክሮ በመስራትና የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ ከድህነት የመውጫ አንዱ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዲሱ ዓመት ፈተናዎችን በመሻገር ወደ እድገትና ሰላም የምንሻገርበት ይሆናል ብለዋል።
አዲሱ ዓመት የመረጋጋትና የተስፋ፣ የሰላም የፍቅርና አብሮነት እንዲሆን ለመላው ኢትዮጵያዊያን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።