ቀጥታ፡

“ለሀገር ህልውና መረጋገጥ የሚከፈል የጀግንነት ዋጋ ክብሩ ታላቅ ነው!”

በ እንግዳው ከፍያለው (ባህርዳር ኢዜአ) 

መሬቱ፣ ሰማዩ እና አየሩ ውሃ የሆነበት ከነፋስ መውጫ እስከ ጨጨሆ የተዘረጋው የተራራ ሰንሰለት እንግዳ ለሆነ ሰው በክረምት ይቅርና በበጋም በቀላሉ ለመላመድ አስቸጋሪ ነው። አካባቢው ከደቡብ ጎንደር ዞን ጉና ተራራ እስከ ሰሜን ወሎ ዞን ድልብ ተራራ የተያያዘ ሰንሰላታማ ከፍተኛ ቦታ በመሆኑም ይታወቃል። 

በዚህ የክረምት ወቅት ከተራራው እየተጥመለመለ የሚወርደው ጉም ሜዳውን፣ ወንዙን፣ ሸለቆውንና ሸንተረሩን ሸፍኖታል። ከተራራው እስከ ሜዳው ላይ የተነጠፈው ጉምም ከርቀት ሲያዩት የተዳመጠ ጥጥ መስሎ ይታያል። በስፍራው የዝናቡን አለማቋረጥ ካስተዋሉት ደግሞ የሰማዩ መስኮት ተከፍቶ ውሎ የሚያድርበት አካባቢ የመጡ ነው የሚመስልዎት።

በዚህ አስቸጋሪ ቦታና ወቅት የሃገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች የተሰባሰቡበት መከላከያ ሠራዊታችን የተፈጥሮም ሆነ አካባቢያዊና መልክዓምድራዊ ተጽዕኖ ትኩረቱ አይደለም። የሃገርን ህልውና ሊያስጠብቅ ሊያፈርሳት ሲኦልም ድረስ ቢሆን እገባለሁ ያለውን አሸባሪ ቡድን ወደተመኘው ስፍራ ሊሸኝ ቆርጦ የተነሳበት ወሳኝ ወቅትም ነው። 

ለዚህ ደግሞ ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል እንደ ሽልማት በመቁጠር የሚሽቀዳደምበት እንጂ ለሰኮንዶች እንኳን የሚደራደርበት ባለመሆኑም የአባቶቹን የጀግንነት ገድል ሊፈጽም ወደፊት ይገሰግሳል። እነሱ በደምና በአጥንታቸው ከውጭ ወራሪና ከውስጥ ጠላት ጠብቀው ያኖሯትን አገር በእኛ ጊዜ ምን ሲደረግ በሚል እልህና ወኔ ያሰበውን እስኪፈጽም የሚያስቸኩለው የዚህ ጀግና ሰራዊት አባላት አካባቢያዊና ተፈጥሯዊ ፈታኝ ሁኔታዎች ቦታም የላቸውም።

እናም ከሰራዊቱ አባላት መካከል ለአካባቢያዊ ቅኝትና ጥበቃ የተመደቡት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ይታያል። ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት ያየ ሰው አገር ማለት የሁሉም ዜጋ ትብብር ውጤት መሆኑን ማጤን ብቻ ሳይሆን እኔስ ለሀገሬ ምን አበረከትኩ? ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ ያደርገዋል። 

በረዶ ያዘለው የአካባቢው ቅዝቃዜ ዓይን አያስጨፍንም፤ እንደልብም አያስገልጥም። እጅ እና እግር የሚተሳሰርበት አስቸጋሪ ቦታ ቢሆንም በመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ላይ የሚታየው የቁርጠኝነትና የጀግንነት ወኔ ግን የአገር ምስጢሩ እዚህ ላይ ነው ያስብላል።

ከርቀት የተጣጠፈ ቀጭን ገመድ መስሎ በሚታየው የጨጨሆ የአስፋልት መንገድ ስትጓዝ አንዱን ኮረብታ ስታልፍ ሌላው ብቅ ማለቱ ጉዞውን የተለየ ያደርገዋል።ጎንደርና ወሎን የሚያገናኘው ብቸኛው የተፈጥሮ ድልድይ ጨጨሆ መድሃኔ ዓለምን አለፍ ብሎ ይገኛል። አካባቢው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ከማራኪ መልክአ ምድር ጋር አጣምሮ የያዘ እንደመሆኑ ይህን እያሰቡ መጓዝ ቀልብን ይስባል።

የመከላከያ ሠራዊትን አዳር፣ ውሎ፣ ማርፈጃና ማምሻ በአካል በቦታው ተገኝቶ ያላየ ሰው በቴሌቪዥን በፉከራና ሽለላ ታግዞ በሚያየው እንቅስቃሴ ብቻ ተንተርሶ ሠራዊት ለአንድ ሃገር ምን ማለት እንደሆነ በአግባቡ ይገነዘባል ብዬ አላምንም። መከላከያ ሠራዊት ለሃገሩ እየከፈለ ያለውን ዋጋና የውትድርና ሙያም ከሙያዎች ሁሉ ቁንጮ ስለመሆኑ ለመረዳት ወደ ግንባር ዘምቶ ማረጋገጥን ግድ ይላል።

ከጨጨሆ መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አለፍ ብሎ እስከ ደብረ ዘቢጥ የተራራ ሰንሰለት ላይ የመሸገውን የአሸባሪው ህወሓትን ታጣቂ አቅም ለማዳከም ከኋላህ የሚተኮሰውን መድፍና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ድምጽ ስትሰማ ውትድርናና የግንባር ውሎ ትርጉሙ በትንሹ ይግለጸልሃል። ምድር ቀውጢ ትሆናለች ጀግንነት በድርጊት ይፈተናል።በዚህ እቶን እሳት ውስጥ የሃገርን ክብርና ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ ገድል ይፈጸማል።በደምና በላብ የተከተበ ደማቅ ድልም ይመዘገባል።

የዚህ ጀግና ሰራዊት አባላት ከባድ መሳሪያዎቻቸው የሚያስወነጭፏቸው የቅጣት በትሮች ተወርውረው የጠላትን ምሽግ በመደርመስ ታጣቂዎቻቸውን ሙትና ቁስለኛ ሲያደርጉ በጦር ሜዳ መነጽር ያያሉ ።ውጤቱ በመገናኛ መልዕክት ሲደርሳቸው በደስታ ይጨባበጣሉ ለሌላ የጀግንነት ተግባርም ይሯሯጣሉ ጊዜ የለም፤ በቃ የእለት ውሏቸው ይሄው ነው።የሃገራቸውን ጠላት ከአፈር መቀላቀል፣ የተመኘውን መስጠት።

በዚህ ግንባር የተሰለፉት የ34ኛ እና 31ኛ ክፍለ ጦሮች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው። እነዚህ ክፍለ ጦሮች ከአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ጠላትን ማስጨነቅ ጀምረዋል።ከሌሎች ክልሎች የመጡ ልዩ ሃይሎችና የጸጥታ አካላት በተሰለፉበት ግንባርም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸው የሚያጠራጥር አይደለም። ምክንያቱም እነሱም የአባቶቻቸው ልጆች የኢትዮጵያ ጀግኖች ናቸውና። በረዶ የተከመረበትን የጉና ተራራ አስቸጋሪ ቅዝቃዜ በመቋቋም ደብረ ታቦር አካባቢ ደርሶ የነበረውን የጠላት ሃይል በአራትና አምስት ቀናት ውስጥ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተውታል፤ፈርጥጦ በመሄድ በጨጨሆ ሰንሰለታማ ተራራ እንዲመሽግም አስገድደውት ነበር።እሱም አልበረከተለትም እንጂ።

የሠራዊቱ አባላት ከማይጸምሪ አካባቢ ተነስተው የመጡና ግዳጃቸው ከዳሎል እስከ ራስ ዳሽን ተራራ የተራራቀ በመሆኑ ስነምህዳራዊ ልዩነቱ ጫና መፍጠሩ የማይቀር ነበር። በአንድ ጊዜ ከበረሃ ወደ ውርጭ ወጥተው የተሰጣቸውን ግዳጅ እንዴት በድል ሊወጡ ቻሉ? የሚለው ጥያቄ በውስጣችሁ ቢያጭር መልሱ የአገር ፍቅር መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል። ምን አልባትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሰላም ማስከበር በሄደበት አገር ሁሉ የአገራችንን ክብርና ዝና ባስጠበቀ መልኩ ተልዕኮውን በአግባቡ የሚፈጽመው ካለው ቁመናና ዝግጅት መሆኑን ይሄ ግዳጅ አንድ ማሳያ ነው። 

ኮሎኔል ያለው አድማሱ የ34ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ተወካይ ናቸው። ሰራዊቱ ምንም እረፍት ሳያደርግና አካባቢውን ሳይላመድ ወዲያው ወደ ጦርነት መግባቱን ይገልጻሉ። ጦርነቱ የሚካሄደው ደብረ ታቦርን በቅርብ ርቀት የሚያየው የጠላት ሃይልና ለሀገሬ አጥንትና ደሜን እሰጣለሁ ባለው የወገን ጦር መካከል ነው። ውጊያው ከደብረ ታቦር በ10ኪሎ ሜትር ያነሰ ርቀት ላይ ተካሂዷል። ኮሎኔሉ እንዳሉት ጠላት የጨበጣ ውጊያ ውስጥ ገብቶ ባልጠበቀው መልኩ ድባቅ በመመታቱ መቋቋም አቅቶት የተረፈው ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ግድ ብሎታል።

የዓይን እማኝ የሆኑ የጎብጎብ አካባቢ ነዋሪዎችም ጠላት ማፈግፈግ ብቻ ሳይሆን ሲዋጋባቸው የነበሩ ታንኮችንና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን እያወደመና እየጣለ ሲፈረጥጥ እንዳዩ መስክረዋል። ክምር ድንጋይ አካባቢ አንድ የጠላት የጦር አመራር ኮሎኔልን ጨምሮ በርካታዎች መማረካቸውንም ያስታውሳሉ።

ሁለቱ ክፍለ ጦሮች እየተጋገዙ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላትን ከደቡብ ጎንደር አካባቢ ጠራርገው ለማስወጣት ጊዜ አልወሰደባቸውም።አሁን ላይ የደብረ ዘቢጥ፣ አግሪት... ከተሞችን ለቆ ወደ ጋሸና እየፈረጠጠ የሚገኘው በሰራዊታችን ጀግንነት፣ የሃገር ፍቅር ስሜት፣ ጽናትና ቁርጠኝነት መሆኑንም ነው የገለጹት። በሰራዊቱ ፋታ የማይሰጥ ጠንካራ ምት የደረሰበት የጠላት ሃይልም ሽንፈቱን አምኖ ለመቀበል ቢከብደው ሌሎች የዘወትር ማወናበጃ ልፈፋውን በራሱና በተላላኪዎቹ ከማስወራት ወደ ኋላ አላለም።

የክፍለ ጦሮቹ አመራሮች ስልት፣ የውጊያ ጥበብ፣ ለሰው ሃብታቸው ያላቸውን ጥንቃቄ…. ለተመለከተ ደግሞ ጦርነት በደመነፍስ የሚካሄድ ሳይሆን የራሱ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ የተከበረ ሙያ መሆኑን ያስገነዝባል። የጨጨሆ ዋሻዎች፣ የተራራው ሰንሰለትና ጫካው ጠላት በአካባቢው የያዘው ገዥ ቦታ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ የወገን ጦር የተለየ ስልት ባይጠቀም ኖሮ አሸባሪው ቡድን ግዙፍ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለማድረስ ተዘጋጅቶ ነበር።

ይህን አስቸጋሪ አካባቢ ለማስለቀቅ መከላከያ ሠራዊታችን በወሰደው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ያለምንም የእግረኛ ውጊያ በየተራራው፣ በየሸለቆውና በየዋሻው መሽጎ የነበረው የጠላት ሃይል ሙትና ቁስለኛ ሆኗል። የተረፈውም ለመፈርጠጥ ነው የተገደደው። የወገን እግረኛ ጦር ያን አስቸጋሪና ሰንሰለታማ የጨጨሆ አካባቢዎች ዘልቆ ደብረ ዘቢጥ አፋፍ ላይ ያለውን የጠላት ምሽግ የተቆጣጠረው ብዙም ሳይቸገር ነው። "ደብረ ዘቢጥ ላይ በተካሄደው ውጊያም የወገን ጦር በከባድ መሳሪያ ድብደባ በመታገዙ በጠላት ጦር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል፤ ለተገኘው ድልም የህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ ወሳኝ ነበር” ብለዋል ኮሎኔል ያለው።

ጠላት በጋሳይ፣ በክምር ድንጋይ፣ ሳሊ፣ ጎብጎብና ነፋስ መውጫ በሚኖሩ ንጹሀን ዜጎች ላይ የፈጸመው ግድያ፣ ግፍና በደል እንዲሁም የሃብትና ንብረት ዝርፊያ በወገን ጦር አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድበት አድርጓል። ሠራዊታችን ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ይህን የጥፋት ቡድን እግር በእግር እየተከታተለ በመደምሰስ የህዝቡን እምባ ማበሱን ከነዋሪዎቹ ስሜት መረዳት ይቻላል። በሀገር የቁርጥ ቀን ልጆች ተጋድሎ ዛሬ ደብረ ታቦር፣ ጋሳይ፣ ሳሊ፣ ጎብጎብ፣ ነፋስ መውጫ፣ ደብረ ዘቢጥ፣ አግሪትና ሌሎች ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረዋል። ምንም እንኳ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው በወራሪው ሃይል የተጎዳ ቢሆንም።

“የእኛ ሃላፊነት ደማችንን አፍስሰን፤ አጥንታችን ከስክሰን፤ ነፍሳችንን አስይዘን… የአገራችን ሰላምና የህዝባችንን ደህንነት ማረጋገጥ በመሆኑ በምናስመዘግበው ድል ኩራት ይሰማናል” የሚለው የ34ኛ ክፍለ ጦር የሰራዊቱ አባል 10 አለቃ እሸቱ አያሌው ነው። “የአመራሮቻችን ቁርጠኝነት በየተሰለፍንበት ግንባር በቀላሉ በድል ላይ ድል እንድንጎናጸፍ አስችሎናል፤ ሰራዊቱ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ የሚያግደው ነገር የለም” ሲል በወኔ ስሜቱን አንጽባርቋል።

ነፋስ መውጫ ከተማ ቀበሌ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ቦሴ ገላው ከአንድ ቤት ሦስትና አራት ንጹሃን ያለምንም ምክንያት በጠላት ሃይል መጨፍጨፋቸውን በጥልቅ ሃዘን ውስጥ ሆነው ይናገራሉ። "የሞቱትን መመለስ ባይቻልም ቀሪ የቤተሰብ አባላትን እምባ ለማበስ ሠራዊቱ የተወጣው ሃላፊነት ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል” ያሉት እኚህ እናት የህወሓት ታጣቂዎች ባለቤታቸውን አቶ ሙላት መንገሻን ከሁለት ወንድሞቹ ጋር በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው ሳይበቃ አስከሬናቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ስለጣሉት ፈልጎ ለመቅበር ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸዋል። 

በሀገሩ ባህልና ወግ መሰረት ሀዘናቸውን ለመግለጽ ማልቀስ እንኳን አልተፈቀደላቸውም። በቤታቸው ሆነው የልቅሶ ድምጽ ሲያሰሙ የህወሓት ታጣቂዎች እየመጡ ያስፈሯራቸው እንደነበር አውስተዋል። “ሶስት ጀግኖችን ባንድ ቀን ቀብረን፤ እንዴት እንባችንን መገደብ ይቻለን?” የሚሉት ወይዘሮ ቦሴ እንባቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በቤተሰባቸው ግፊት ወደ ገጠር ሄደው ሃዘናቸውን መግለጻቸውን ነው የገለጹት። ወደ ቤታቸው የተመለሱትም ጠላት አካባቢያቸውን ለቆ ወጣ ሲባል ነው። የአገሬ ሰው “እየዬም ሲደላ ነው” የሚለው ለእዚህ አይደል!

ወይዘሮ ቦሴ አሁን ላይ በመከላከያ ሰራዊትና በሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በተወሰደ የተቀናጀ ርምጃ የጠላት ሃይል ተንኮታኩቶ መውደቁን ሲሰሙ ከሀዘናቸው ተጽናነተዋል። "ከመጽናናቴ የተነሳ የባለቤቴና የወንድሞቹ ደም እንደተመለሰ እቆጥረዋለሁ" ብለዋል።

ጠላት በደረሰባቸው ከተሞች ከትላልቅ ህንጻዎች እስከ አነስተኛ የኮንቴነር ሱቆች አውድሟል። የመንግስትና የግለሰቦችን ሃብትና ንብረትም ዘርፏል። በዚህም ዛሬ ሰርቼ ቤተሰቤን እረዳለሁ፣ ነገ የራሴን የኑሮ ደረጃ እለውጣለሁ ብለው በመፍጨርጨር ላይ የነበሩ የስራ እድል ተጠቃሚ ወጣቶችን ሳይቀር ህልማቸውን አምክኖታል።

ባንኮች፣ የጤና ተቋማት፣ ኮሌጆች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማትና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በውስጠቸው የነበሩ ቁሶች በዚህ ነፍሰ-በላ የሽብር ቡድን ሙሉ በሙሉ ተዘርፈዋል። ቡድኑ ጠቃሚ መስሎ ያልታየውንም አውድሟል። በግለሰብ ቤት ሳይቀር ዱቄት፣ ጤፍና ሌሎች የእህል አይነቶችና ንብረቶችንም ጭኖ ወስዷል። 

“የአሸባሪው ቡድን የፈጸመው ግፍና በደል በእኛ ይብቃ” ያሉት ወይዘሮ ቦሴ፣ የጥፋት ቡድኑን በጋራ ተሰልፎ በመደምሰስ የአገራችንን ሰላም ማረጋገጥ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ነው የገለጹት። ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ዓመታት የተሰራበትን የመከፋፈል ሴራ በመበጣጠስ አሁን የጀመረውን ህብረትና አንድነት ማጠናከር እንዳለበት ይመክራሉ።

የአገር መከታና አለኝታ መከላከያ ሠራዊት በወኔ እየፈጸመ ያለውን የአባቶቹን የጀግንነት ተግባር ሁሌም መዘከር ያስፈልጋል። ወጣቱ ትውልድም ከሠራዊቱ ጎን በመስለፍና መከላከያን በመቀላቀል የአባቶቹን የጀግንነት ታሪክ የሚደግምበት ጊዜው አሁን ነው።ለዚህም እያሳየ ያለውን ዝግጁንት ማጠናከር አለበት። የህወሓት የሽብር ቡድንም ሆነ ሌሎች ጠላቶች ወደ መቃበር እንዲወርዱ ወጣቱ ትውልድ የመከላከያ ሰራዊት ወንድሞቹን አሻራ መከተል ይኖርበታል። መቼም ቢሆን ለሃገር ክብር የሚከፈል ዋጋ በታሪክ ተመዝግቦ ሲዘከር ይኖራል፤ሞቱም ከክብር በላይ ክብር ነው። ለሀገር ህልውና መረጋገጥ የሚከፈል የጀግንነት ዋጋ ክብሩ ታላቅ ነው።የጀግና ልጆች ኢትዮጵያም ዘላለማዊ ክብሯን ጠብቃ ትኖራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም