ለዘማች የሠራዊት አባላት ቤተሰቦች የአዲስ ዓመት መዋያ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘማች የሠራዊት አባላት ቤተሰቦች የአዲስ ዓመት መዋያ ድጋፍ ተደረገ
ባህር ዳር፤ ጷጉሜን 4/2013 (ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለዘማች የሠራዊት አባላት ቤተሰቦች የአዲስ ዓመት መዋያ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉን ያደረገው በሴት አመራሮች፣ በምሁራንና በነጋዴ ሴቶች የተመሰረተው “የዘመኑ ጣይቱ” የተሰኘ ማህበር መሆኑ ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊና የማህበሩ መስራች ወይዘሮ ብዙአየሁ ቢያዝን ፤ማህበሩ የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅና በመልሶ ማቋቋም የላቀ ሚና ለመጫወት መመስረቱን በወቅቱ ገልጸዋል።
ከተመሰረተ አንድ ወር ያልሞላው ማህበር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማሰባሰቡን ተናግረዋል።።
በእዚህም ከ4ሺህ 200 በላይ ቦርሳ እና የውሃ መጠጫ ኮዳ ለአማራ ልዩ ሃይል አባላት ልጆች ድጋፍ መደረጉን አውስተዋል።
ትናንት ደግሞ በወረታ የሚገኙ ጉዳት የደረሰባቸው የሠራዊት አባላትን መጎብኘታቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ብዙአየሁ፤ በ200ሺህ ብር ለዘማች ቤተሰቦች የዓመት በዓል መዋያ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
በእዚህም ለ40 የዘማች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው የበግ ፣ 25 ኪሎ ግራም የጤፍ ዱቄት፣ የበርበሬና የሽንኩርት ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።
ሴት ነጋዴዎችን ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ጽጌ ግርማ በበኩላቸው፤ ማህበራቸውን በማጠናከርና በማደራጀት የተጀመረውን ድጋፍ እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።
"አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ለጆሮ የሚዘገንን ግፍ መፈጸሙን እየሰማን ነው" ያሉት ወይዘሮ ጽጌ፣ ለተጎዱ ወገኖች ፈጥኖ ለመድረስ ከወዲሁ ሃብት እየተሰባሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፤ አሸባሪው ህወሓትን ለመደመሰስ የዘማች ቤተሰቦችንና በግንባር የተሰለፈውን ሠራዊት መደገፍ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
"ድጋፉ ሠራዊቱ ከቤተሰብ ትዝታ ወጥቶ ሙሉ ትኩረቱን ለሀገር ክብርና ለዜጎች ደህንነት ብቻ እንዲያደርገ ያስችለዋል" ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በግንባር ላይ ለሚገኘው ሰራዊት የዓመት በዓል መዋያ የበሬ ሰንጋ፣ የበግና የፍየል ሙክት እንዲሁም ሌሎች ቁሶች ን ዛሬ ልኳል ብለዋል ዶክተር ድረስ።
ወደ ግንባር ለተላኩ ከ300 በላይ የሚሊሻና የምልስ ሠራዊት አባላት ቤተሰቦችም በከተማ አስተዳደሩ የበዓል መዋያ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
“የዘመኑ ጣይቱ” የተባለው ማህበር ገና ከመቋቋሙ ለሠራዊቱ አባላት ቤተሰብ ድጋፍ ማድረጉ ለህልውና ትግሉ የደጀንነት ሚናው እየተወጣ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፤ በእዚህም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የዘማች ቤተሰቦችም ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።