ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ደማቅ በጀግንነት ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፤ አሁንም እየጻፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ደማቅ በጀግንነት ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፤ አሁንም እየጻፉ ነው
ዻጉሜን 4/ 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ደማቅ በጀግንነት ታሪክ ጽፈው አልፈዋል፤ አሁንም እየጻፉ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደረጃ የጀግንንት ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያዳታ፣የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ አባት አርበኞች እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ጽፈዋል፤ የአሁኑ ትውልድም ይህን እያስቀጠሉ ነው።
የማይታለፍ የሚመስለውን ችግር አልፈናል፣በየዘመኑም የጋራ ጠላቶቻችንን አሸንፈናል ነው ያሉት።
የባንዳ ጥንካሬ የሚፈጠረው በጀግኖች ዝምታ ነው፣ጀግኖች ሲነሱ ባንዳ ይጠፋል ይህንን በተግባር አይተናል ሲሉም ጠቁመዋል።
ብርሃን ሲበራ ጨለማ እንደሚጠፋ ሁሉ፤ ጀግኖች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ባንዳዎች ያለመታሰቢያ ከታሪክ ማህደር ተነቅለው ይወገዳሉ ብለዋል።
በጀግንነት የመኖር ሚስጥር ከፍረሃት ወጥቶ በድል ምንጣፍ ላይ መራመድ የመቻል ልምምድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እኛ ኢትዮጵያውን በረዥም ዘመን የሀገር ግንባታ ታሪካችን የጀግንነት ልምዳችን ብዛትና ስብጥር አያሌ ወረቶችን እንድናካብት መልካም እድል ፈጥሮልናል ብለዋል።
በጀግንነት አስተሳሰብ ስሪት ያካበትናቸውን ወረቶች ለበለጠ ድል መጠቀም እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናግረዋል።
ጅግንነትን ማክበር ተጨማሪ ጀግኖችን ለማፍራት ምቹ መደላድል መፍጠሪያ መንገድ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ጀግኖችን የምታፈራ ማህፀነ ለምለም ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያ በጀግኖቿ ተከብራ ትኖራለች ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጀግኖችን በማፍራት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
እየተጠናቀቀ ባለው የ2013 ዓመት በእናት ጡት ነካሾች የሀገር ክብር በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ የክህደት ጥቃት ቢፈጽሙም በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ትግል ችግሩን ተሻግረነዋል ብለዋል።
ጀግንነት ጊዜና ጉልበትን ለሀገር ጥቅም በማዋል እንደሚገለጽም ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ህይወታቸውን ለህዝባቸው እየሰጡ ያሉ ጀግኖች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
በመዲናዋ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጀግኖችን ቅድሚያ በመስጠት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመርሃ ግብሩ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በገንዘብ፣180 ሚሊየን በዓይነት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ድጋፉንም ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ አስረክበዋል።
በተጨማሪም 350 ሚሊየን ብር ለአማራ ክልል እና 170 ሚሊየን ብር ደግሞ ለአፋር ክልል ድጋፍ አድርጓል።