የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስከበር ለከፈላችሁት መስዋዕትነት እናመሰግናለን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስከበር ለከፈላችሁት መስዋዕትነት እናመሰግናለን
አዲስ አበባ፣ ዻጉሜን 4/ 2013 (ኢዜአ) ''የኢትዮጵያን ሕልውና እና ዳር ድንበር ለማስከበር እየከፈላችሁት ላለው መስዋዕትነት ከፍተኛ አክበሮት አለን፤ እናመሰግናለን'' ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ 'የጀግንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በጦር ሃይሎች ኮንፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝተው በሕክምና ላይ የሚገኙ የሰራዊት አባላትን አበረታተዋል።
አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለሰራዊቱ አባላት አምስት ሰንጋ በሬዎችንና 28 በጎችንና ፍየሎችንም በስጦታ አበርክተዋል።
ፕሬዚዳንቷ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ''ለኢትዮጵያ ሕልውና መስዋትነት እየከፈሉ ካሉ ጀግኖች ጋር በማሳለፌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ የአገር መከታ የሆኑት የሰራዊት አባላት በጀግንነት መስዋእትነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።
የአገራችን ደጀን የሆነው እኛ እንድንኖር፣ ወጥተን እንድንገባ፣ ሰላም እንዲከበር እየተጋ ባለው ሰራዊታችን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት በቀላሉ የሚታለፍ ባለመሆኑ የተከፈለ መሰዋዕትነት መሆኑንም ገልጸዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ትልቅነት ጠብቆ ለዚህ ያበቃና ከድንበሯ አልፎ ለሌሎችም ጭምር የተረፈ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
''የኢትዮጵያን ሕልውና እና ዳር ድንበር ለማስከበር እየከፈላችሁት ላለው መስዋዕትነት ከፍተኛ አክብሮት አለን፤ እናመሰግናለን'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህልውና እንዲቀጥል ከአሁኑ ሁኔታ ትምህርት በመውሰድ መተባበርና በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።
ለአገር ህልውና ሲሉ መስዋእትነት እየከፈሉ ላሉ የሰራዊት አባላት አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍና እውቅና እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ''ለአገራችሁ ነጻነት፣ ክብርና አንድነት መስዋዕትነት የከፈላችሁ በመሆናችሁ ታላቅ ክብር ይገባችኋል'' ብለዋል።
''በዚህ ዕለት ከጀግኖች ጋር ከመዋል በላይ ክብር የለም፤ የሰራችሁት ታሪክም ለትውልድ የሚተላለፍ ነው፤ እናንተ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጀግኖች ናችሁ'' ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
በሕክምና ላይ የሚገኙ የሰራዊቱ አባላትም ለኢትዮጵያ ሕልውና እና ዳር ድንበር መከበር ለከፈልነው ሁሉ ክብር ይሰማናል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በጀግንነት የኖሩ ሕዝቦች መሆናቸውን አስታውሰው በዚህ ዘመን በጀግንነት ለኢትዮጵያ መሰለፋችን ያኮራናል ሲሉ ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ዶክተር ሀይሉ እንዳሻው ''ለኢትዮጵያ ክብር መስዋዕትነት ከከፈሉ ጀግኖች ጋር 'የጀግኖችን ቀን' ማሳለፋችሁ ያስመሰግናችኋል''ተብለዋል።