ምንም እንኳን በፈተናዎች የታጀበ ዓመት ቢሆንም 2013 በዲፕሎማሲው መስክ ስኬት የተመዘገበበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምንም እንኳን በፈተናዎች የታጀበ ዓመት ቢሆንም 2013 በዲፕሎማሲው መስክ ስኬት የተመዘገበበት ነው
አዲስ አበባ፤ ዻጉሜን 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዓመቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን የተጋፈጠች ቢሆንም የዲፕሎማሲው መስክ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው ኢትዮጵያ ባሳለፍነው አመት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያገኘቻቸውን ስኬቶችና ፈተናዎች አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከፈተናዎቹ ቀዳሚው የታላቁን ህዳሴ ግድብ የፀጥታ ሁኔታ የተመለከተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የህወሃት ወራሪ ኃይል በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በድንገት የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በአገሪቱ ላይ የተደቀነውን የሉዓላዊነት ስጋት ለማስወገድ መንግስት የወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ስኬታማ እንደነበርም አስታውቀዋል።
በመንግስት ላይ ከውጭ እየደረሰ ያለው ያልተገባ ተፅእኖና ግፊት እንዲሁም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መንግስትን በተመለከተ የሚነዙት የተዛቡ ዘገባዎች ረገብ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
አንዳንድ አለም አቀፍ ማህበረሰቦች አሸባሪውን ህወሃት ደግፈው ያቀረቡበት መንገድ አንዱ ችግር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ባደረገው ያለሰለሰ ጥረት በመጨረሻም ቢሆን ማህበራዊ ሚዲያውን አቅጣጫ በማስያዝ አሸባሪውን ቡድን በፈጸመው ጥፋት ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ቡድኑን ለመውቀስ ቀደም ብለው ሲያንገራግሩ የነበሩ አንዳንድ አካላት የቡድኑን የተሳሳተ አካሄድ ቢዘገይም በአደባባይ እንዲያወግዙ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ለስድስተኛ ጊዜ የተከናወነው አገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ ለአየር ፀባይ ለውጥ ባበረከተው አስተዋጽኦ ያገኘው እውቅና የኢትዮጵያ የድል ዜና ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያና ሱዳንን የድንበር ጉዳይ በማስመልከት ሁኔታዎች በነበሩበት መንገድ መቀጠላቸውንና ኢትዮጵያ ጉዳዩን በታላቅ ጥንቃቄ እየተከታተለችው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በነዚህ ሁሉ ስኬቶች መሃል ፈተና አለመጥፋቱንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የዓለም አገራት መውጫ አጥተው የተቀመጡ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የተደረገው ጥረት በፈተናዎች ቢታጀበም ስኬት እንደታየበት አስታውቀዋል፡፡
በመስከረም መጨረሻ የሚመሰረተው አዲሱ መንግሰት፣ የሚመለከታቸውን ሁሉንም አካላት ያቀፈ ምክከር ማድረግ፣ በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልል የተጎዱ ወገኖችን ሰላም መመለስ ቀዳሚ ስራው እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን የጦር መሳሪያ አጓጉዟል በማለት በአገሪቱ ባለስልጣናት የተነዛው የሀሰተኛ ወሬ የአየር መንገዱን ስም ለማጠልሸት ያለመ ቢሆንም ያልተሳካ ሙከራ ነበር ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡
በቤልጂየምና ሉክሰምበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የሚከናወነውን የልማት ስራ ለመደገፍ የሚረዳ 800 ሺህ ዶላር፣ በኮሎራዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 100 ሺህ ዶላር መስጠታቸውን አስታውሰዋል።