ቀጥታ፡

በአዲሱ አመት በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ የሚያካክሱ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ - አቶ አገኘሁ ተሻገር

ባህር ዳር ፣ ጳጉሜ 4/2013 ''በአዲሱ ዓመት የህወሃት ወራሪ ሃይል በከፈተው ጦርነት የተጎዳውን የክልሉ ኢኮኖሚ ማካካስ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ ይከናወናሉ '' ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታውቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ለአዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጰያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላልፈዋል።

አቶ አገኘሁ በእንኳን አደረሳችሁ መግለጫቸው እንዳሉት በ2013 በተለይም አይችሉም አያደርጉትም የተባለው ሃገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ አሸናፊ ሆነው እንዲጠናቀቅ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

“የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው ለማደናቀፍ ቢሞክሩም በበሰለ አካሄድ ማከናወን የተቻለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ዓመት እንዲሆን አድርጎታል “ ሲሉም አመልክተዋል።

በውስጥ ጉዳያችን ጭምር ጣልቃ በመግባት ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሞከሩ ሃገራት አጀንዳቸው የከሸፈበትና በውጭ ዲፕሎማሲ ታላቅ ስኬት የተገኘበት ዓመት እንደሆነም ጠቁመዋል።

“ይሁን እንጂ የትህነግ ወራሪ ሃይል አማራን ለማዳከምና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በመከላከያ ሰራዊት ላይ እርምጃ በመውሰዱ የከፈተው ጦርነት በሁሉም መስክ በተፈለገው ልክ እንዳንጓዝ አድርጓል” ብለዋል።

ወራሪ ሃይሉ አማራን እንደ ህዝብ በማዳከምና በማጥፋት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይዞት የተነሳው ግብ በበሳል አመራርና በህዝቡ ጠንካራ ርብርብ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል:: 

“ይሁን እንጂ አሸባሪው ሀይል በወረራቸው አካባቢዎች ንፁሃንን ያለምንም ርህራሄ በጭካኔ ገሏል፣ ሃብታቸውን ዘርፏል፣ ያልቻለውን በማውደም ለአማራ ያለውን ጥላቻ አሳይቷል” ብለዋል።

እንዲሁም የህክምና፣ የመንግስት የአገልግሎት ተቋማትንና የድርጅቶችን ማንኛውንም ንብረት በደረሰበት ሁሉ በመዝረፍ ልክ አልባ በደል መፈፀሙን ተናግረዋል።

በተለይም በአማራ ክልል በማይካድራ፣ ጭና፣ አጋምሳ እንዲሁም በአፋር ክልል ጋሊኮማ የፈፀመው ግፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ያስደነገጠና በታሪክ የማይረሳ መሆኑን አመልክተዋል።

አሸባሪው ሀይል በወረራቸው አካባቢዎች ከ551 ሺህ በላይ ህዝብ ለችግር መጋለጡን ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

“አሸባሪው ሀይል በእብሪት ተነሳስቶ በከፈተው ጦርነት በጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች ልዩ ሃይሎች፣ በሚሊሻና በመላው ህዝቡ ርብርብ በገባበት ሁሉ እየተቀበረ ይገኛል” ብለዋል።

“ወራሪ ሀይሉ ዳግመኛ ጦርነት እንዳያስብና ለአማራም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስጋት እንዳይሆን አድርጎ በመቅበር በአዲሱ ዓመት የተጀመሩ ስራዎች በአጠረ ጊዜ የማጠናቀቅ ስራ ይሰራል” ሲሉም አስታውቀዋል። 

በአዲሱ አመት አሸባሪ ሀይሉ በወረረባቸው አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መልሶ ማቋቋምና የወደሙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ከመገንባት ጎን ለጎን በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ማካካስ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወኑ ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

በክልሉ ጦርነቱ በሌለባቸው አካባቢዎች ጠንካራ የግብርና ስራ ማከናወን እየተቻለ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ ከወራሪው ሃይል በተለቀቁ አካባቢዎች ደግሞ በቀሪ እርጥበትና የመስኖ ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

“ለመስኖ ልማቱ ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በማቅረብ የተሻለ ስራ እንዲከናወን ይደረጋል” ብለዋል።

“አዲሱ ዓመት አዲስ መንግስት የሚቋቋምበት ዓመት ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በሁሉም መስክ የተጀመሩ ስራዎች በተሻለ ጥንካሬና ቅልጥፍና እንዲከናወኑ ያግዛል” ብለዋል።

ህዝቡ አዲሱን ዓመት ሲያከብር በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ፣ አቅመ ደካሞችንና ኑሮ የከበዳቸውን በመደገፍና በማገዝ እንዲሁም ማዕድ በማጋራት እንዲሆን አሳስበዋል።

አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማት፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተጋገዝ እንዲሁም ችግሮችን በትጋት የምንሻገርበት የተስፋ ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ሲሉም የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም