የወረዳው ህዝብ ለመከላከያና ሌሎች ጸጥታ ሀይሎች ለበዓል መዋያ ድጋፍ አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የወረዳው ህዝብ ለመከላከያና ሌሎች ጸጥታ ሀይሎች ለበዓል መዋያ ድጋፍ አበረከተ
ደሴ ጳጉሜን 4/2013 (ኢዜአ) በሰሜን ሸዋ ዞን የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ህዝብ ለመከላከያ ስራዊትና ለሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሰንጋዎችና በጎችን በድጋፍ አበረከተ።
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ታዬ ዛሬ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን ለሚታገለው ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ያለንን አጋርነትን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
የዞኑ ህዝብ ከዚህ ቀደም በርካታ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው "ዛሬ ደግሞ የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ህዝብ ለበዓል መዋያ 40 ሰንጋዎችና 2 ሺህ 445 በጎችን ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል።
ከወረዳው ህዝብ በተሰበሰበ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
አሸባሪው ቡድን እስኪቀበር ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ምክትል አስተዳዳሪው "የቡድኑ እድሜ እንዲያጥር ሁሉም በሚችለው አቅም አስተዋፅጾ ማድረግ ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ እንዳሉት "ለስራዊቱና ፀጥታ አባላት የሚደረገው ድጋፍ ብርታትና ወኔ ከመስጠቱም ባለፈ አንድነታችንን በተግባር ያሳየ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡
የደቡብ ወሎ ዞንም በጥሬ ገንዘብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይና 50 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለሃገር ህልውና እየተዋደቀ ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል እገዛ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ህዝብ ያደረገው ድጋፍ የማይረሳ መሆኑን ጠቁመው ሌሎችም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል ።
የህወሀት ወራሪ ኃይል በደቡብ ወሎ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች በቅንጅት የሚደርስበትን ምት መቋቋም ባለመቻሉ መፈርጠጡን ምክትል አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።
በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።