ቀጥታ፡

''ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ በጀግንነት መሰዋዕት መሆን ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ክብር ነው'' - ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሃብተማሪያም

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4/2013(ኢዜአ) ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ በጀግንነት መሰዋዕት መሆን ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ክብር መሆኑን የቀድሞ ሠራዊት የአየር ወለድ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሃብተማሪያም ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሺ አመት በሚቆጠር ታሪኳ ከእራሳቸው በላይ ለሀገራቸውና ወገናቸው ቅድሚያ በመስጠት ጀብዱ የሰሩ በርካታ ጀግኖችን ያፈራች ማህጸነ ለምለም ሀገር ናት።

ጀግንነት በተለያዩ መስኮች የሚገለጥ ሲሆን፤ በአውደ ውግያ የሚፈጸመው ጀብዱ ግን በተለየ መልኩ የደምና የህይወት መሰዋዕትነት የሚጠይቅና በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ለሀገርና ወገን የሚከፈል ዋጋ ነው።

ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ታሪክ ቅብብሎሽ ነጻና የረሷ አኩሪ ታሪክ ያላት ሀገር አስጠብቀው ለአሁኑ ትውልድ አስተላልፈዋል።

በቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ በአውደ ውግያ ሜዳ ታላቅ ጀብዱን  ከፈጸሙ የሜዳሊያ ተሸላሚ ጀግኖች መካከል የቀድሞ የአየር ወለድ የጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም አንዱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጷጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከበረውን የጀግንነት ቀንን  አስመልከቶ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም ቆይታ አድርገዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም በዚሁ ወቅት፣ በየትውልዱ ለሀገርና ለህዝብ  ሲባል የሚከፈል ዋጋ እንደሚኖር ተናግረዋል።

ሀገራቸው በሰጠቻቸው ግዳጅ በተሳተፉበት አውድ ውጊያ በታማኝነትና በታላቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ሀገራቸውን እንዳገለገሉም ያስታውሳሉ።
በተለይ በ1970 ዓ.ም በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት በተለይ በጠላት ቀለበት ውስጥ የነበሩትን ሀረርና ድሬደዋን ለማስለቀቅ  ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው የፈጸሙትን ጀግንነት ዘወትር እንደሚያስታውሱት ይናገራሉ።
ጀግንነት በሁሉም የሙያ ዘርፍ የሚገለጽ ነው ያሉት ብርጋዴር ጀነራሉ፤ በውትድርና የሙያ ዘርፍ ያለው ጀግንነት ግን በተለየ መልኩ የህይወት፣ የአካልና የደም  መሰዋዕትነት የሚከፈልበት ነው ሲሉም ይገልጻሉ።

የሰው ልጅ በህይውት ውጣ ውረድ ውስጥ በተለያዩ ስኬቶች ደስታን ሊያጣጥም ይችላል ያሉት ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም፤ ከምንም ነገር በላይ ለሀገርና ህዝብ መስዋእትነት እንደመክፈል ክብርን የሚያጎናጽፍ የለም ነው ያሉት።

ለሀገር ፍቅር ሲሉ ሶስት ጊዜ እንደቆሰሉ ገልጸው፤ ይህም ለሀገሬ ነጻነት እና ለህዝቤ አንድነት የከፈልኩት ዋጋ ነው ብለዋል

"ምንም ነገር ማድረግ የሚቻለው ሀገር ሲኖር ነው" ሲሉም ሀገር ያላትን ዋጋ ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድ ለኢትዮጵያ ህልውና ዘብ በመቆም ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ነጻ ሀገር ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለበትም አንስተዋል።

አሁን ኢትዮጵያን የገጠማት ችግሮችም ጊዜያዊና የሚያልፉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ወጣቶች ሀገራቸው ከእነርሱ የምትጠብቀውን ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መጪው አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያ ሰላም የሚበዛበት ዘመን አንዲሆን በመመኘት ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም