መጪው የበዓል አከባበር ሀገርን ለማዳን እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊትና ቤተሰቦች በማሰብ ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መጪው የበዓል አከባበር ሀገርን ለማዳን እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊትና ቤተሰቦች በማሰብ ሊሆን ይገባል
ሀዋሳ ፤ ጳጉሜን 04/2013 (ኢዜአ) አዲሱን ዓመት በመቀበል በዓሉን ስናከብር ሀገር ለማዳን በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊትና ቤተሰቦቻቸውን በማሰብ ሊሆን ይገባል የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ 2013 ዓ.ም. በፈተናዎች ውስጥም ቢሆን አኩሪ ድሎች የተመዘገቡበት ዘመን ነው።
የተገባደደው ዓመት የሀገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ሀይሎች ተቀናጅተው ሀገር ለማፍረስ የተነሱበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ምርጫውን ሰበብ በማድረግ ሀገር ለማተራመስ ወጥነው በነበረበት ወቅት በሳሉ የሀገራችን ህዝብ የምርጫውን ሂደት ፍጹም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በማከናወን የሚበጀውን በመምረጥ የሀገሪቱን አንድነት አስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባት ተችሏል ነው ያሉት አቶ ደስታ።
ሀገሪቱን ለዓመታት ሲበዘብዝ የቆየው አሸባሪው ህወሀት በምርጫው ትርምስ ለመፍጠር ያሰበው አልሳካ ሲለው ከውጪ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ ጦርነት መክፈቱንም አመላክተዋል።
ይህን ጦርነት ለመመከት የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ልዩ ሀይሎችና ሚሊሻዎች በጋራ በመሆን በዱር በገደሉ እየተዋደቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የሰራዊቱን ተጋድሎ ለማገዝም መላው ህዝብ ከጎኑ መሆኑን በገንዘብ፣ ደም በመለገስና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
ህዝቡ እያደረገ ካለው ድጋፍ አንድነቱን ጠብቆ በመቀጠል ሀገሩን መጠበቅና የተጀመረውን ሰላም የማስከበር ስራ በማገዝ ዴሞክራሲና ብልጽግናን ለማምጣት መስራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እያጋጠመን ያለው ችግር ወቅታዊ መሆኑን በመረዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዚህ ለመውጣት መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በተለይ አዲሱን ዓመት ስናከብር የራስ ደስታ የሁላችን መሆኑን በመረዳት ሀገርን ለማዳን በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ያለውን ሰራዊትና ቤተሰቦቹን ማሰብ ይኖርብናል ብለዋል።
አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በሚቻለው ሁሉ በማገዝ በዓሉን የጋራ ማድረግ እንደሚገባም እንዲሁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታ ፣ የስኬትና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።