የግል ዘርፉ እንዳያድግ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንቅፋት ሆነዋል---ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
የግል ዘርፉ እንዳያድግ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንቅፋት ሆነዋል---ጥናት
አዲስ አበባ ነሓሴ 8/2010 የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የግል ሴክተሩ ውጤታማ ሆኖ እንዳይወጣ ጫና እየፈጠሩ መሆኑ ተመለከተ። 'በመንግስት ተቋማት ያለው የመልካም አስተዳደር ሁኔታና የግሉ ልማት' በሚል የተጠና ጥናት ነው ይህን ያለው። ጥናቱን ያስጠናው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሲሆን ጥናቱን ለማጽደቅ የተለያዩ የመንግስትና የዘርፉ ባለድርሻዎች የተሳተፉበት አውደ ጥናት ዛሬ ተጀምሯል። ጥናቱን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር አቶ መሰንበት አሰፋ እንዳሉት የመንግስት ተቋማት በግሉ ዘርፍ ላይ የሚያስከትሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች መለየትና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ማሳየት ማዕከል አድርጎ ነው ጥናቱ የተጠናው። "ብዙ አገራት ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ የቻሉት የግሉን ዘርፋ በማሳተፍ ነው" የሚሉት የጥናቱ አቅራቢ በኢትዮጵያ ግን የግል ዘርፉ በህግ የተሰጠውን መብት መጠቀም በማይችልበት ደረጃ የመልካም አስተዳደር በደሎች እንደሚደርሱበት ተናግረዋል። የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው "የግል ዘርፉን ውጤታማ ከሚያደርገው አንዱ የብድር አቅርቦትና ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ነው" የሚል ነው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ነው የተባለው የውጪ ምንዛሪ እጥረት አንዱ ቢሆንም በተለይ ግን የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለባቸው የመልካም አስተዳደር ብልሹነትና ሙስና ዘርፉን እንዳይራመድ ካደረጉት መካከል እንደሚገኙበት አቶ መሰንበት ገልፀዋል። በጥናቱ እንደተመለከተው መልሳቸውን ከሰጡ 200 ሰዎች 53 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የህግ የበላይነትን አክብረው አይሰሩም። በሌላ በኩል 96 በመቶ የሚሆኑት እንዳሉት በተቋማቱ ሙስና ስር የሰደደና በተቀመጠው ህግ መሰረት የሚፈለገው አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጓል። ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ቢፒአር፣ ካይዘንና ሌሎች የለውጥ መሳሪያዎች ተግባራዊነትም አናሳ ነው። የዓለም ባንክ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በጎሮቤት አገር ኬንያ ካሉት የግሉ ዘርፍ 41 በመቶ በባንክ ብድር የሚጠቀሙ ሲሆን በኡጋንዳ ደግሞ 22 በመቶ ናቸው። በኢትዮጵያ ካሉት የግሉ ዘርፎች መካከል ግን 16 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው በባንክ ብድር አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉት። ከዚህም ሌላ ጥናቱ የታክስ አስተዳደር ፍትሃዊ አለመሆኑንና በታክስ አስተዳደር የተቀመጡ ህጎች በተጠቀሱት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተግባራዊ እየተደረጉ አለመሆኑን አሳይቷል። በጥናቱ ላይ በተሰጠው ምክረ-ሃሳብ በመታገዝ መንግስት የግሉን ዘርፍ በመደገፍ አገሪቱ የጀመረችውን የኢንዱስትሪ ጉዞ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆን እንዳለበትም ተገልጿል። ዘርፉ እንዴት መመራት እንዳለበት የሚያሳይ የግል ዘርፍ ብሄራዊ ስትራቴጂም መዘጋጀት አለበት ተብሏል። የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እርስ በራሳቸው ከመናበብ ጀምሮ ቢሮክራሲያቸውን መቀነስ አለባቸው የሚል ምክረ ሃሳብም ተቀምጧል። በአይሲቲ የታገዘ አገልግሎት መስጠትን ማበረታታት እንዳለበትም ነው የተጠቆመው። የምክር ቤቱ ዋና ፀኃፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ ጥናቱ ሃሳባችንን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመንግስት ለማቅረብ ታስቦ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ግብዓት የሚጠይቅ በመሆኑ መንግስት ከመሰረተ ልማት ጀምሮ ህግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ የግል ዘርፉን መደገፍ አለበት ብለዋል። በተለይም በህግ የተቀመጡ መብቶችን ለመጠቀም አላስችል ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ አለበት ሲሉ ተናግረዋል። ጥናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በ13 ከተሞች ላይ የተካሄደ ሲሆን ከመንግስትና ከግል ተቋማት 200 በሚሆኑ ሰዎች በተገኘ ምላሽ የተሰራ ነው። አውደ ጥናቱ እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን በቀረበው ጥናት ላይ ሃሳብና አስተያየት ተካቶበት አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታትና ህጎችን ለማሻሻል ለመንግስት የሚቀርብ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።