ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር በአሸናፊነት እንድትወጣ ድጋፋችን መቀጠል ይኖርበታል- ዶክተር አፀደ ተፈራ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር በአሸናፊነት እንድትወጣ ድጋፋችን መቀጠል ይኖርበታል- ዶክተር አፀደ ተፈራ
ደሴ፤ ጷጉሜን 04/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ውስብስብ ችግር በአሸናፊነት እንድትወጣ ድጋፋችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ ተናገሩ።
ለሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ለበዓል መዋያ ግምታቸው ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ሰንጋ በሬዎች ፣ በጎችግ፣ የእህልና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፉን ያደረጉት የወሎ፣ ደብረ ብርሃን እና የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ናቸው፡፡
ሦስቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋታል።
ከእነዚህ ውስብስብ ችግሮች በአሸናፊነት እንድትወጣም ዜጎች በተለይ ወጣቱ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ አሸባሪውን ህወሓት መደምሰስና ተፈናቃዮችን መደገፋቸውን አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያሉት።
"ህወሓት ግብአተ መሬቱ እስኪፈጸም ድረስ ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንዳቸውን ማጠናከርና በጥፋት ቡድኑ የሚደርሰውን ጉዳት በጋራ መመከት ይኖርብናል" ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ለህዝብ ያላቸውን አጋርነት በተግባር እያሳዩ መሆኑን ጠቁመው፣ በድጋፉ የወሎ፣ መቅድላ አምባ እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
እንደ ዶክተር አፀደ ገለጻ ፤ ከድጋፉም 30 ሰንጋ በሬዎች፣ 60 ኩንታል ስንዴና ጤፍ፣ 500 ብርድ ልብስ እንዲሁም 745 ሊትር የምግብ ዘይት ይገኙበታል።
"አሸባሪውን ህወሓት ምንም ሳንዘናጋ ተረባርበን መቅበር ይጠበቅብናል" ያሉት ደግሞ የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ወልደማሪያም ናቸው።
በሀገር ማፍረስ ተግባር የተሰማራው ህወሓት በኢትዮጵያዊያን ህብረት እስኪወገድ ድረስ በጋራ መመከት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ለሠራዊቱና ለተፈናቃዮች የዘመን መለወጫ በዓል መዋያ እንዲሆን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው 200 በጎችና የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ አድርጋል።
"ለህልውና ዘመቻው የሚደረግ ድጋፍ ሀገርና ህዝብን ከወራሪና አሸባሪው ቡድን የማላቀቅ አጀንዳ በመሆኑ እስከድል ማግስት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
ለሠራዊቱ የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት በመከላከያ ሚኒስቴር የሰሜን እዝ የሎጅስቲክ፣ ቀለብና ንብረት መምሪያ ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ቢያ አባቦር ናቸው።
ሌተናል ኮሎኔል ቢያ ድጋፉን ከተረከቡት በኋላ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ የአሸባሪውን ቡድን ዕድሜ ለማሳጠር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።
በግንባር እየተፋለመና ውድ ህይወቱን እየገበረ ላለው ሠራዊት እየተደረገ ያለው ደጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ ፣ በተቋማቱ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።፡
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡንና ተቋማትን በማስተባበር ለተፈናቃዮች የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያዊያን የተጀመረው ድጋፍ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።
በጥፋት ቡድኑ ወረራ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ፣ ኮምቦልቻና አካባቢዋ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ224 ሺህ በላይ መሆናቸውን ተጠቅሷል፡፡