የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የጋምቤላ ክልል ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የጋምቤላ ክልል ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ጷጉሜን 04 2013 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ለሀገር መከላከያና ለሌሎች የጸጥታ ሀይሎች የሚያደረጉትን ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሰታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ ዓመት ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝብ የድልና የልማት ዘመን እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ መግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ ከአሁን በፊት የክልሉ መንግስትና ህዝብ ለሀገር መከላከያና ሌሎች የጸጥታ አካላት በሰው ሃይል፣ በገንዘብ ፣ ደም በመለገሰና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደረጉ ቆይተዋል።
በአዲሱ ዓመትም ህወሓት፣ ሸኔና ሌሎች የጥፋት ተላላኪዎችን እኩይ ሴራ ተቀልብሶ የህልውናው ዘመቻ በድል እስኪጠናቀቅ የጋምቤላ ህዝብ ህዝባዊ ደጀንነቱንና ድጋፉን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም የውስጥና ውጭ ጠላቶች በሀገር ላይ የተጋረጠውን ፈተና በድል በመሻገር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ህዝቡን አስተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቅሴዎች ተግዳሮት እየሆነ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከሉ ተግባርም ሌላው በአዲሱ በጀት ዓመት በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን ነው የገለጹት።
ቀደም ሲል በክልሉ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅና የክልሉን ሰላም አስተማማኝ የማድረግ ተግባርም የአዲሱ ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።
2013 ዓ.ም. እንደ ሀገር ፈተናዎች የበዙበት ዓመት ቢሆንም በርካታ የድል ስኬቶች የተመዘገቡበት እንደነበርም አውስተው አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚወገዱበትና የሚያፍሩበት፤ የክልሉ ብሎም ሀገሪቱ ህዝቦች ደግሞ የሚደሰቱበት ዘመን እንዲሆን ርዕሰ መሰተዳደሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።