በደቡብ ወሎ ዞን ሁሉም አካባቢዎች ደስታን ለመግለጽ ጥይትም ሆነ ርችት መተኮስ ክልክል ነው...የዞኑ አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ዻጉሜን 04 /2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ሁሉም አካባቢዎች ደስታን ለመግለጽ ጥይትም ሆነ ርችት መተኮስ የተከለከለ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሀመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ  ዛሬ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀይቅና ደሴን ለመቆጣጠርና ለመዝረፍ በማሰብ በተሁለደሬና ወረባቦ ወረዳዎች ወረራ ለማድረግ ሞክሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን በመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና በህዝቡ ብርቱ ክንድ ተደምስሶ ቀሪው ደግሞ ወደመጣበት ተመልሷል ነው ያሉት።

በዚህም የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ደስታቸውን ጥይት በመተኮስ  ሲገልጹ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በሽብር ቡድኑ ላይ እንጂ በከተሞች ለደስታ የሚተኮስ ጥይት መኖር የለበትም ብለዋል።

በመሆኑም በደቡብ ወሎ ዞን ሁሉም አካባቢዎች ደስታን ለመግለጽ ጥይትም ሆነ ርችት መተኮስ የሚከለክል መመሪያ መተላለፉንም ተናግረዋል።

መመሪያውን በመጣስ ጥይት በሚተኩሱ ግለሰቦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ላይ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም