ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በበዓሉ ዋዜማ ከግሪድ የሚወስዱትን ኃይል እንዳይጠቀሙ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ዻጉሜን 04 ቀን 2013 (ኢዜአ) በውጭ ንግድና በሲሚንቶ ዘርፍ ከተሰማሩ በቀር ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ከግሪድ የሚወስዱትን ኃይል በበዓሉ ዋዜማ እንዳይጠቀሙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጠየቀ።

የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ የዘመን መለወጫ በዓል መዳረሱን ተከትሎ በሃይል አጠቃቀም ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ እጥረቶችና ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን መከወኑን ለኢዜአ ገልጿል።

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘመን መለወጫ በዓል የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ለማሟላት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በዚህም የኤሌክትሪክ መስመሮች ጥገናዎችና ማስተካከያዎች መደረጋቸውን ገልፀዋል።

በበዓል ዋዜማና በዕለቱ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ብልሽት ቢያጋጥም አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ ተጠበባቂ ሠራተኞች እንደሚኖሩም አስታውቀዋል።

በበዓሉ ሳቢያ የሚጨምረውን የሃይል ፍላጎት ለማሟላት በኤክስፖርትና በሲሚንቶ ዘርፍ ከተሰማሩ በስተቀር ኢንዱስትሪዎች ከግሪድ የሚወስዱትን ኃይል በበዓሉ ዋዜማ ባለመጠቀም እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡም ቀደም ብለው ሊዘጋጁ የሚችሉ ነገሮችን በማከናወን በበዓሉ ዋዜማና ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል መጨናነቅ እንዳይፈጠር የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ የምግብ ማብሰያዎችን ከምሽቱ 3:00 ሠዓት በኋላ እንዲጠቀሙም አቶ መላኩ መክረዋል፡፡
አቶ መላኩ ህብረተሰቡ ከኤሌክትሪክ ጋር የተገናኘ አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም