ቀጥታ፡

ከመቅደላ ተዘርፈው የነበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር ሊመለሱ ነው

ጳጉሜን 4፤2013 (ኢዜአ) በ1868 በመቅደላ ጦርነት ወቅት ተዘርፈው የነበሩ መንፈሳዊ፤ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር ሊመለሱ መሆኑን በለንደን የኢፌዴሪ ኤምባሲ አስታውቋል።

ኤምባሲው ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ ቅርሶቹን ሼሄራዛድ(Scheherazade) በመባል ከሚታወቀው የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩል መረከቡን ነው የገለጸው።ቅርሶቹን ለመረከብ ወራትን የወሰዱ ድርድሮችን እና ለሽያጭ ቀርበው የነበሩትን ከገበያ እንዲነሱ በማድረግ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚመለሱ ተገልጿል።

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ቅርሶቹ ለሀገር ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ሌሎች በዘረፋ የተወሰዱትን በዚህ መልክ በድርድር ለማስመለስ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል።

ከቅርሶቹ መካከል የጦር ጋሻ፣ ከቆዳ የተሰራና በእጅ የተጻፈ የብራና መፅሀፍ ቅዱስ ፣ጽዋ የሚወሰድበት ዋንጫ ከነማንኪያዎቹ፣የጳጳስ አክሊል እና የቀንድ ዋንጫዎች እንደሚገኙበት ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም