ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውን ህወሃት በአንድነት እየደመሰሱት ነው - ዶክተር ቀንአ ያደታ

ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር አሸባሪውን ህወሓት እየደመሰሱ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንአ ያደታ ገለጹ።

ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያበረከተውን 60 ሚሊዮን ብር ዛሬ ተረክበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ሠራዊቱ እያደረገ ላለው ተጋድሎ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አጋርነቱን ለመግለጽ ድጋፉን እንዳደረገ ተናግረዋል።

ድጋፉ ከአካዳሚክ ሠራተኞች የአንድ ወር፣ ከአስተዳደር ሠራተኞች ደግሞ የግማሽ ወር ደመወዝ የተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው አሸባሪው ቡድን አፈናቅሏቸው በደሴ አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች ግምቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ቁሳቁሶችን ማበርከቱን ገልጸዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ በቀጣይም በአፋርና ሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው ዝግጅት ተደርጓል።

የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር የሙያና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋለ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀንአ ያደታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሰው ሃይል ልማት፣ በጥናትና ምርምርና ሌሎች ዘርፎች ከሚያከናውናቸው ስራዎች ጎንለጎን ለመከላከያ ሠራዊት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በተመሳሳይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች እስካሁን 240 ሚሊዮን ብር በአይነትና በገንዘብ ለሠራዊቱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ዋነኛ ተልዕኮው ኢትዮጵያን መበታተን እንደነበር አውስተዋል።

በአገራቸው አንድነት ድርድር የማያውቁት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክረው ዳር እስከዳር በመነሳት አሸባሪውን ቡድን እየደመሰሱት መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም አሸባሪው ቡድን እንደፈለገው ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ ከሽፎ የኢትዮጵያ አንድነት መጠናከር መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም