ቀጥታ፡

የጉብኝት መርሃ ግብሩ ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ያለውን አጋርነት የሚያሳይበት ነው

ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) የዳያስፖራው የጉብኝት መርሃ ግብር ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ አለኝታ መሆኑን በተግባር የሚያሳይበት አጋጣሚ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ገለፀ።

መርሃ ግብሩን የሚያስተባብረው የምክር ቤቱ የልዑካን ቡድን አባላት "አባይን እንጎብኝ እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁትን መርሃ ግብር አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አለባቸው ደሳለኝ፤ "በመርሃ ግብሩ ከተለያዩ ክፍለዓለማት የተውጣጡ 500 ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይሳተፋሉ" ብለዋል።

በቆይታቸውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለበትን ደረጃ እንደሚጎበኙና በግድቡ ግንባታ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞችን እንደሚያበረታቱ ተናግረዋል።

የገበታ ለሸገርና ገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች ጉብኝት እንደሚካሄድና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሙዚየም ለመክፈት የመሰረት ድንጋይ እንደሚቀመጥም ጠቁመዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ፣ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነት ለማሳየትም የደም ልገሳ መርሃ ግብር እንደሚካሔድ ነው አቶ አለባቸው የገለጹት።

ዳያስፖራው መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚመሰረተው መንግስት ያለውን አጋርነት የሚገልጽበትና አደራ የሚሰጥበት የቃልኪዳን እራት እንደሚያዘጋጅም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሙን የሚያሳይበት ትዕይንተ ሕዝብ በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ የስካንዲኒቪያን አገራት አስተባባሪ ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ "ኢትዮጵያ ምጥ ውስጥ ናት ከምጧ መገላገል አለባት" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ዳያስፖራው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

"ለዳያስፖራው በመልካም ጊዜ ወደ አገሩ መምጣት ምንም ላይሆን ይችላል" ያሉት ወይዘሮ ኢትዮጵያ፤  በችግሯ ጊዜ ከጎኗ መቆም አለኝታነት እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የአውሮፓ አገራት አስተባባሪ አቶ ዘውዱ መንግስቴ ዳያስፖራው ከጉብኝቱ ባለፈ በቀጣይ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋዩን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

"ዳያስፖራው ገንዘብና እውቀቱን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለማሳደግ ከመንግስት ጋር በቅርበት ይሰራል" ብለዋል።

በጉብኝቱ የሚሳተፉ ዳያስፖራዎች ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመለሱ ለተቀረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ እንደሚያስረዱም አክለዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው "ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በመጎብኘት የምትገኝበትን ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትና የቱሪዝም አምባሳደር ሆኖ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲያስተዋውቅ እንፈልጋለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከመገንባት አኳያም የዳያስፖራው ሚና ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም