ቀጥታ፡

ለአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ አገሩ እንዲመለስ ጥሪ ቀረበለት

አዲስ አበባ ነሓሴ 8/2010 በ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን የብር ሜዳሊያ ለአገሩ ያስገኘው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ አገሩ እንዲገባ ጥሪ ቀረበለት። ወደ አገሩ ሲገባም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሎምፒክ ኮሚቴ የጀግና አቀባበል ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በ2016 ሪዮ ኦሎምፒክ ላይ በማራቶን ኢትዮጵያን ወክሎ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ አገሩ ተመልሶ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ፍሬያማ ውጤት እንዲያበረክት ነው ጥሪ የቀረበለት። አትሌቱ አገሪቱን በልዩ ልዩ የዓለም አትሌቲክስ መድረኮች በመወከልና ከፍተኛ ውጤት በማስመገብ ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አስተዋጽኦ አድርጓል። በመሆኑም "አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ አገሩ በመመለስ የተለመደውን ፍሬያማ ውጤት ለአገራችን እንዲያበረክት ፍላጎታችን በመሆኑ የጀግና አቀባበል ለመቀበል ዝግጁ መሆናችን እንገልጻለን" ብለዋል ሁለቱ ተቋማት በመግለጫቸው። በሪዮ ኦሎምፒክ በወንዶች ማራቶን ለኢትዮጵያ የብር ሜዳልያ ያስገኘው ፈይሳ ሌሊሳ በወቅቱ ውድድሩን ለመጨረስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩት፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች መንግስትን በሚቃወሙ ሰልፎች ላይ በብዛት የታየውን ምልክት በማሳየት ውድድሩን ማጠናቀቁ ይታወሳል። ይህንን የተቃውሞ ምልክት በመሳየቱ ከወቅቱ የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ወደ አገሩ ሳይመለስ ወደ አሜሪካ ማቅናቱም ይታወሳል። በወቅቱም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አትሌቱ ባሳየው የተቃውሞ ምልክት ወደ አገሩ ቢመጣ ምንም የደህንነት ስጋት እንደማይገጥመው መግለጹ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም