ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ የሕዝቦቿን እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት የምትሻበት ጊዜ ነው

ጷጉሜ 03 ቀን 2013 (ኢዜአ) "አገራችን ኢትዮጵያ ትብብራችንን እና ድጋፋችንን የምትሻበት ጊዜ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ይህን ያሉት የተለያዩ ተቋማት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ባደረጉበት ስነ ስርዓት ላይ ነው።

የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽንና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር 11 ሚሊዮን፣ አለርት ሆስፒታል 6 ሚሊዮን፣ ከድር አሊ ጄኔራል ትሬዲንግ 500 ሺህ፣ ኢትዮ-ኮንሰልታንት ኢንጂነሪንግ 255 ሺህ ብር፣ ሶራ ሴክዩሪቲ 106 ሺህ ብር አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ደግሞ 200 ሺህ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

ተቋማቱ አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ እየተጋ ለሚገኘው ሠራዊት ከገንዘብ ባሻገር ባሏቸው በሙያና ሌሎች ድጋፎች ከጎኑ እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት ኢንጅነር አይሻ "አገራችን ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንንና ትብብራችንን የምትሻበት ጊዜ በመሆኑ አሸባሪውን ቡድንና አስተሳሰቡን ማስወገድ አለብን" ብለዋል።

"ወንድማማችነታችንንና ድጋፋችን ለሠራዊቱ ከፍተኛ ሞራል ይሆነዋል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሕዝቡም ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያውያን አንድነት የበለጠ እንዲጠናከር ማድረጉን የገለጹት የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አስፋ፤ "አሁን ያለው የኢትዮጵያዊነት መነሳሳትና አንድነት ለወዳጆቻችን ደስታ ለጠላቶቻችን ደግሞ መረብሽን ፈጥሯል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያለችበትን የፈተና ወቅት በአንድነትና በመተባበር ማለፍ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለአገር ክብር በግንባር የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ የጸጥታ ሃይሎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናከሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት በበኩላቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠው፤ ከገንዘብና ከዓይነት ድጋፍ በተጨማሪ ባላቸው ሙያ ለሰራዊቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት እያደረገው ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖታል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም