አሜሪካ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የቲቢ መመርመሪያ ማሽን ድጋፍ አደረገች

120

ጳጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) አሜሪካ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የቲቢ በሽታ መመርመሪያ ማሽን ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገች።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ 46 የቲቢ መመርመሪያ ማሽን ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።

ማሽኖቹን የተረከቡት ዶክተር ሊያ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ቲቢን በምርመራ የመለየት አቅም 71 በመቶ መድረሱንና በዚህም በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነስ እንደተቻለም ተናግረዋል።

በድጋፍ የተሰጡት ማሽኖች በአገር አቀፍ ደረጃ ቲቢ የመመርመር አቅምን የሚያሳድጉና አገልግሎቱን የሚያቀላጥፉ እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡

ዶክተር ሊያ የአሜሪካ መንግስት የኮቪድ ወረርሽን ለመከላከልና ለሌሎች ተግባራት ለሚያደርገው እገዛ  አመስግነዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በበኩላቸው ድጋፉ የሁለቱን አገራት ሕዝቦች የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

መመርመሪያ ማሽኖቹ ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመከላከል የምታደርግውን ጥረት በእጅጉ የሚያገዙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የአሜሪካ መንግስት በልማት ትብብርና በጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ጊታ ፓሲ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም