ምዕመኑ በአዲሱ ዓመት ችግርና ፈተናዋን የተሻገረች ኢትዮጵያን ለማየት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ምዕመኑ በአዲሱ ዓመት ችግርና ፈተናዋን የተሻገረች ኢትዮጵያን ለማየት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል
አዲስ አበባ ጷጉሜ 3/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን አብሮነታቸውን በማጠናከርና ለሠላምና ለይቅርታ በመዘጋጀት በአዲሱ ዓመት ችግርና ፈተናዋን የተሻገረች አገር እንድትኖር የበኩላቸውን እንዲወጡ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
ኢትዮጵያ በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት በርካታ ለውጦችና ስኬቶችን አስመዝግባለች፤ በአንጻሩ እድገቷን በማይሹ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ጦርነትን ጨምሮ የተጋረጡባትን ችግሮችና ፈተናዎች ለመሻገር በትግል ላይ ትገኛለች።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶችም እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት በአገሪቷ በርካታ ሁነቶች መከሰታቸውን ያወሳሉ።
በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት የደረሰውን የንጹሃን ሞት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም አንስተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ግጭቶችም ተጠቃሽ ክስተቶች ነበሩ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊና የድሬዳዋና ጅቡቲ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ሕዝበ ምዕመኑ አዲሱን ዓመት በመልካም ተግባራት ለመቀበል ከወዲሁ ማሰብና መዘጋጀት አለበት ይላሉ።
አዲሱ ዓመት በተለይም ፈታኝ የሆኑትን ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይና የኮቪድ ወረርሽኝ ችግሮች ለመፍታት ከፈጣሪም ምህረት የሚለመንበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ምዕመኑ ሕዝብ አብሮነቱን በማጠናከርና ለይቅርታ ዝግጁ በመሆን በአዲሱ ዓመት ከችግርና ከፈተና የተላቀቀች አገርን ማየት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ "በሰዎች የሕይወት ጉዞ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣሪን የመማጸኛ ምክንያቶች ናቸው" ይላሉ።
ኢትዮጵያ አሁን እያሳለፈችው ያለው ሁኔታም ይህንኑ የሚያመለክትና ፈጣሪ ጎንበስ ብሎ ምድሪቱን እንዲጎበኝ ልመናና ተማጽኖን የሚጠይቅ ክስተት ነው ብለዋል።
"ኢትዮጵያ የአማኞች አገር ሆና እነዚህን ተደራራቢ ችግሮች እያሳለፈች መሆኗ አንድ ምክንያት አለው" ያሉት ፓስተር ፃዲቁ አዲሱ ዓመት እርቅን፣ ይቅር ባይነትንና አብሮነትን ይዞ እንደሚመጣ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
"ሰዎች የኖሩበትን ዘመን በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመረዳዳትና በአብሮነት ሲያሳልፉ ፈጣሪም የሚመጣውን አዲስ ዘመን ይባርካል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማ ምክር ቤት አባልና የሠላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼኽ መሀመድ ሲራጅ ናቸው።
ኢትዮጵያ ባጋጠማት ችግር ሳቢያ በዜጎቿ መካከል ቂም በቀልና ጥላቻ እንዳይኖር በየትኛውም እምነት የተጠለለ ፈጣሪውን ለሠላምና ለአብሮነት መማጸንና ለዚሁ መዘጋጀት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሁሉም ሃይማኖት እርቅን፣ ሠላምና መተባበርን ይሰብካሉ ያሉት ሼኸ መሀመድ በአዲሱ ዓመት ፈጣሪ የሚደሰትበትና ምሕረት የሚሰጥበትን በጎ ተግባር በመፈፀም ጥንታዊቷን ኢትዮጵያን መመለስ ያሻል ነው ያሉት።
አዲሱን ዓመት "በአዲስ መንፈስና በአምላካዊ ትዕዛዝ መቀበል ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ጽህፈት ቤት የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ኃላፊ አባ ዳንኤል ካሰው ናቸው።
ለችግርና ለፈተና ምላሽ ለማግኘት ፈጣሪን በጸሎትና በምህላ መለመን ብቸኛው አማራጭ ነው ያሉት አባ ዳንኤል ዕድሜ አግኝቶ ደስታውን፣ ፈተናውንና ችግሩን ማየትም በራሱ መታደል ነው ብለዋል።
በዚህ አገራዊ ሁኔታ ውስጥ ማለፍና ለትውልዱ ታሪክ ለመናገር መብቃት ትልቅ ሃላፊነት መሆኑን ተገንዝቦ አገሪቱ ከገባችበት ፈተና ለማውጣት ምዕመኑ አሻራውን ማኖርና ግዴታውን መወጣትም ይጠበቅበታል።
ለዚህም ሁሉም ከፈጣሪው እርቅን በመለመን በመጪው አዲስ ዓመት ከችግርና ከፈተና የጸዳች ኢትዮጵያን ማየት ሊናፍቅ ይገባል ነወ ያሉት አባ ዳንኤል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የጳጉሜን አምስት ቀናት በሁሉም ቤተ እምነቶች ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር ከፈጣሪ መፍትሄ ለማግኘት ያወጀችው ጸሎትና ምህላ እየተካሄደ ነው።