ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው--የጃፓን አምባሳደር

82

ጳጉሜ 3/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እናደንቃለን ሲሉ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ተናገሩ።

አምባሳደሯ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ጉዞ በፈጣን ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ጃፓንን ጨምሮ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ግዜ እየዳበረ መምጣቱም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የአገርን ሉአላዊነት የማስከበር ሂደቱ ከገጠማት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉም አምባሳደሯ ገልጸዋል።

የተለያዩ ችግሮች በማደግ ላይ ያሉም ሆነ ያደጉት አገራትን ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቅሰው፤ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተና ታልፈዋለች ብለዋል።

አምባሳደሯ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማት፣ የፍቅርና አንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።

በአዲሱ ዓመትም ችግሮች ሁሉ ተወግደው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ ልማት፣ፍቅርና አንድነት እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ግንኙነቷን ይበልጥ የምታጠናክረበት እንደሚሆንም እምነቴ የፀና ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ጃፓን የትብብር ግንኙነት ከ90 ዓመታት በላይ የዘለቀና አሁንም በጠንካራ ወዳጅነት የቀጠለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም